የትግራይ ክልል ቀውስ እንዲያበቃ ከተፈለገ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆም አለበት-- የታሪክ ተመራማሪ ዴቪድ ስቴይንማን - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል ቀውስ እንዲያበቃ ከተፈለገ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆም አለበት-- የታሪክ ተመራማሪ ዴቪድ ስቴይንማን
ነሀሴ 28 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የትግራይ ክልል ቀውስ እንዲያበቃ ከተፈለገ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆም አለበት” ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ዴቪድ ስቴይንማን ገለጹ።
ዴቪድ ስቴይንማንየታሪክ ተመራማሪ ሲሆኑ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ሬገን አስተዳደር የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ነበሩ። ላለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ንቅናቄ ከፍተኛ የውጭ አማካሪ በመሆን የሰሩ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት በኢትዮጵያ ሲፈጸሙ የነበሩ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች፣ ዘረፋዎችና የሃብት ምዝበራዎችን በታላላቅ ዓለም አቀፍ ጋዜጦችና መጽሄቶች ሲያጋልጡ የቆዩ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ፈጽመዋቸዋል ለተባሉት ወንጀሎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ክስ በመመስረት ይታወቃሉ።
እኒህ የታሪክ ምሁሩ በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው “Getting It Wrong in Ethiopia’s Tigray” በሚል ርእስ ባስነበቡት ጽሑፍ በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ እንዲረግብ ካስፈለገ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
የታሪክ ተመራማሪው እንደሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሀገሪቱ ላይ የተደቀነውን የደህንነት አደጋ ለመጋፈጥ ትግል እያደረጉ ባሉበት ሁኔታ አንዳንድ ምእራባውያን ሀገራት የህወሓት ቡድን ከመንግስት ጋር እኩል እንደሆነ በማሰብ የሚያደርጉት ያልተገባ ጫና ጉዳዩ ይበልጥ እንዲወሳሰብ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ ወደዚህ ቀውስ የገባችው አሸባሪው የህወሃት ቡድን በጫረው ጦርነት ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት ተመራማሪው ይህንን መረዳት ያልፈለጉ ሀገራት፣ ቡድኖችና ግለሰቦች በ1970ዎቹ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ድርቅ ምክንያት የተከሰተው አሰቃቂ እልቂት እንዲደገም ፍላጎት እያሳዩ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ለሰብአዊ እርዳታ ስርጭት መንገዶች ይከፈቱ ከሚለው ዘመቻ ይልቅ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጰያ መንግስት አስፈላጊውን የሎጂስቲክስ፣ የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ እና የሞራል ድጋፍ መስጠት አለበት ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ሕወሓት ቡድን ታጣቂዎች እንዳይሸጋገር የሚያስችሉ ስልቶች መተግበር አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።
የሰብአዊ መብቶች መከበር ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ እንዳልሆኑና የኢትዮጵያ መንግስትም የሚታዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ያብራሩት ተመራማሪው፤ በንጹሃን ደም እጃቸው የቆሸሸው የአሸባሪው ድርጅት መሪዎች ለፍትህ ካልቀረቡ ሰላም ከማሳጣታቸውም በላይ የሰብአዊ መብቶች ጥያቄዎቹ ሙሉ አይሆኑም ብለዋል።
ለመንግስት አስፈላጊውን እርዳታ አድርጎ ችግሮቹን ከመፍታት ይልቅ ኢትዮጵያ ላይ ጫና በማብዛት የሚመጣው ውጤት አፍራሽ ከመሆን ባለፈ የበርካታ ንጹሃንን ህይወት አደጋ ላይ በመጣል ለሰላም መስፈን የሚደረገውን ጥረት ዋጋ በማሳጣት መፍትሄውን ያርቀዋል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።