ህዝቡ ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመረውን ድጋፍ ሊያጠናክር ይገባል---ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታዬ ምናለ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝቡ ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመረውን ድጋፍ ሊያጠናክር ይገባል---ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታዬ ምናለ
ባህር ዳር (ኢዜአ) ነሀሴ 28/2013-- ህዝቡ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ጠላትን በግንባር እየተፋለመ ላለው የፀጥታ ኃይል የሚያደርገውን ድጋፍ ሊያጠናክር እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ አስገነዘቡ ።
በፌዴራልና በክልል የሚገኙ ሴት አመራሮች እንዲሁም ባለሃብቶችና ነጋዴ ሴቶች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ በግንባር ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታዬ ምናለ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት የአሸባሪውና ወራሪው ህወሓት እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ለማስቆም ያልተቋረጠ ድጋፍ ያስፈልጋል።
"ቀደምት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ከጣልያን ወረራ ለመታደግ የፈፀሙት አኩሪ የጀግንነት ገድል በደምና በአጥንት የሚተላለፍ መሆኑን የአሁኑ ትውልዱ እየፈጸመ ያለው ተግባር ጥሩ ማሳያ ነው" ብለዋል።
እናቱ ያጀገነችው ልጅ ግንባሩን ከመስጠት ውጪ ወደኋላ እንደማይመለስ የገለጹት ወይዘሮ ሽታዬ፣ "ህወሓት የፈፀመብንን ወረራ በጀግኖች ልጆቻችን መክተን ብልጽግናን እናረጋግጣለን" ብለዋል።
"ስንተባበርና ስንደመር ኃይል እንሆናለን ብለን በማሰብ በግንባር እየተዋደቁ ለሚገኙ ሴት የሠራዊት አባላት፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ የሚሆኑ የተለያዩ ቁሶችን ድጋፍ አድርገናል" ሲሉም ገልጸዋል።
የህወሓትን የጥፋት ቡድን በማሸነፍ ወደ ነጻነትና ብልፅግና እንሄዳለን በሚል የተጀመረው የበጎ ተግባርም በቀጣይ እንደሚቀጥል ወይዘሮ ሽታዬ ጠቁመዋል።
ህዝቡ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ጠላትን በግንባር እየተፋለመ ላለው የፀጥታ ኃይል የሚያደርገውን ድጋፍ ሊያጠናክር እንደሚገባ ምክትል አፈ ጉባኤዋ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ሴቶች በየዘመኑ ጠላትን በመፋለም ኢትዮጵያን ከጠላት እየታደጉ ይገኛሉ" ብለዋል።
አሁንም የጣይቱ ልጆች አሸባሪው ትህነግ የፈፀመብንን ወረራ ከወንድሞቻቸው ዕኩል በየበረሃው በመዋደቅ ጠላትን እየተፋለሙና ድል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
"በቀጣይም ኢትዮጵያዊያን ሀገርን ለመበተን የተነሳውን ወራሪ ኃይል በአጭር ጊዜ ድል ለማድረግ እጅ ለእጅ መያያዝና በህብረት መቆም ይኖርብናል" ብለዋል።
ለጀግኖች ከሚደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በግንባር ሠራዊቱን ማበረታታት እንደሚፈልጉ የተናገሩት ደግሞ የድጋፍ ሃሳቡ አመንጭና አስተባባሪ ወይዘሮ ትልቅሰው ገዳሙ ናቸው።
"ከቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ እንደ እናትና እንደ እህት ከጎናቸው ሆነን ምግብ በማቅረብ ጀግኖቻችንን ማበረታታትና ማጀገን አለብን "ብለዋል።
በድጋፍ ማሰባሰብ ስራው አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ሃብት በማሰባሰብ ለሴት ወታደሮች የሚሆን 4ሺህ 200 ቦርሳ፣ የንፅህና መጠበቂያና የበሶ መበጥበጫ ዕቃዎችን ገዝተው ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
የዘማች ቤተሰቦችም በዓልን እንደ ሌላው ህብረተሰብ ተደስተው እንዲያሳልፉ ለማድረግ ድጋፍ የማሰባሰቡ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ልዩ ኃይል ሎጂስቲክስ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ እሸቴ በበኩላቸው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በአሸባሪው የተቃጣብንን ጦርነትና ወረራ በአጭር ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ ህዝቡና ባለሃብቱ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
ድጋፉ በግንባር ለሚፋለመው የጸጥታ ሀይል በአግባቡ እንደሚደርስ አስታውቀዋል።