በበጀት ዓመቱ 106 ከተሞች የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ

58

ጋምቤላ፣ ነሐሴ 27/2013( ኢዜአ) ኢትዮ-ቴሌኮም በተያዘው በጀት ዓመት የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ የኢንተርኔት አገልግሎቱን በማስፋት 106 ከተሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ኩባንያው በደቡብ ምዕራብ ሪጅን በጋምቤላ ከተማ የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ አገልግሎት ዛሬ በይፋ በማስመረቅ ስራ አስጀምሯል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በስነ -ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ወደ ሌሎች ከተሞችም ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ።

በተያዘው በጀት ዓመትም የተጀመሩ የማሻሻያ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በሀገሪቱ የሚገኙ 106 ከተሞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል የተካሄደው የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንድ የሞባይል ኢንተርኔት ማሻሻያ አገልግሎቱን ፈጣንና አስተማማኝ ለማድረግ ታሰቦ የተሰራ መሆኑን ጠቁመው የተካሄደው ማስፋፊያ ከ93 ሺህ በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

አድቫስንድ የ4ጂ በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ የዋለው በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2020 መሆኑን የጠቆሙት ስራ አስፈፃሚዋ ቴክኖሎጂው በተለይም ሀገሪቷ የያዘችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ በማሳለጥ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጀሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የ4ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ የኢንተርኔት አገልግሎቱን በላቀ ደረጃ የሚያሻሻል ቴክኖሎጂ በመሆኑ የክልሉ ህዝብና መንግስት ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶታል።

ቴክኖሎጂው በተለይም የክልሉን ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢከኖሚያዊ የልማት ስራዎችን በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም