የኢትዮጵያን ክብር፣ ስምና ዝና ለማስጠበቅ ከመከላከያ ጎን እንቆማለን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ክብር፣ ስምና ዝና ለማስጠበቅ ከመከላከያ ጎን እንቆማለን
ሚዛን ነሀሴ 27/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ክብር፣ ስምና ዝና ለማስጠበቅ ከመከላከያ ጎን እንቆማለን፤ እስከ ህይወት መስዋዕትነትም ዋጋ እንከፍላለን ሲሉ የምዕራብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አጋርነታቸውን የገለጹበትን ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በጀሙ ከተማ አካሂደዋል። በህዝባዊ ሰልፉ በጥሬ ገንዘብና በአይነት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰብስቧል።
መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት ለሀገርና ለህዝብ ሲሉ በግንባር እየከፈሉ ላሉት መስዋዕትነት አክብሮታቸውን የገለጹት ሰልፈኞቹ፣ ለሠራዊቱ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አድርገዋል።
"የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አርማችንና መለያችን ነው" በማለት በሰልፉ ላይ ድምጻቸውን ያሰሙት ነዋሪዎች፣ በሀገር ጉዳይ የሚመጣን ለመመከት ለመከላከያው ደጀን እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።
በተለያየ መንገድ የጀመሩትን ድጋፍ በቀጣይም እንደሚያጠናክሩ የገለጹት የሰልፉ ተሳታፊዎች ለሀገር ክብር፣ ስምና ዝና እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋጂዋ ሳፒ ለሰልፉ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት "የኢትዮጵያውያን ትልቁ ክብራችን በሀገር ጉዳይ አለመደራደራችን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመድፈር የሞከረ ሁሉ አፍሮ መመለሱን ያስታወሱት አስተዳዳሪው፣ "የህወሓት የጥፋት ቡድን አፍሮ የሚመለስ ብቻ ሳይሆን ከአፈር ተቀላቅሎ ይቀራል" ብለዋል።
የዞኑ ህዝብ በግንባር እየተፋለሙ ለሚገኙ የመከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ አካላት በሁለተኛ ዙር 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መቱ አኩ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ኢትዮጵያ ትላንትም ያልተደፈረች ኩሩ ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።
"ዛሬ እናፈርሳታለን በሚል ጋብቻ ፈጥረው የተነሱ ባንዳና ከሃዲዎችን በአንድነት ቆመን እናጠፋለን" ሲሉም አክለዋል።
በሁለተኛ ዙር የዘማቾች ምልመላ ከ300 በላይ ፈቃደኛ ወጣቶችን መመዝገባቸውን የተናገሩት አቶ መቱ ፣ የዞኑ ህዝብ በገንዘብና በቁሳቁስ ጭምር ድጋፉን እያጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው የድጋፍ ሰልፍ ለህልውና ዘመቻው 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬና በአይነት ድጋፍ ከመደረጉ በተጨማሪ 19 በሬዎች፣ 32 ፍየል እና በግ እንዲሁም 50 ኩንታል ስንዴና ደረቅ ስንቅ ከህዝቡ መሰብሰቡንም አቶ መቱ ተናግረዋል።
ድጋፉ የህወሓት የጥፋት ቡድን ግብዓተ መሬት እስኪፈጸም ድረስ ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ብርሃኑ ዲማ፣ "የጁንታው ቡድን ላይመለስ ተቀብሮ እስኪጠፋ ድረስ ድጋፋችንን ያለ ያለመሰልቸት እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግሯል።
"ጦርነቱ የመኖር አለመኖር ጉዳይ ስለሆነ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነኝ" ያሉት ደግሞ አቶ ጌታቸው አባተ የተባሉ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ ናቸው።
ከሰው ባለፈ እንስሳትን በመግደልና መሠረተ ልማት በማውደም ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ህወሓት ከምድረ ገጽ ማጥፋት ካልተቻለ ሰለም አይገኝም ሲሉም ተናግረዋል።