ቀጥታ፡

በከተሞች እየተባባሰ የመጣው የአየር ብክለት በሰዎች ላይ ከፍተኛ የጤና እክል እያስከተለ ነው

ነሀሴ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) በከተሞች እየተባባሰ የመጣው የአየር ብክለት በሰዎች ላይ ከፍተኛ የጤና እክል እያስከተለ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ገለጸ።

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሸንና ከአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የቡድን መሪ ወይዘሮ ፋንቱ ክፍሌ፤ ከተሸከሪካሪዎች የሚወጣው ጪስ በመዲናዋ ከፍተኛ የአየር ብክለት እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል።

እኤአ ከ2013 እስከ 2016 በአዲስ አበባ የነበረው የአየር ብክለት መጠን አሁን ላይ በ50 በመቶ ከፍ ብሏል ብለዋል።

የአየር ብክለቱ አይነተኛ መንስኤ የተሸከርካሪዎች ጭስ መሆኑን ጠቅሰው በሰዎች ላይ ከፍተኛ የጤና እክል እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ለማ በበኩላቸው፤ ከተሸከርካሪዎች የሚወጣው ጪስ በከባቢ አየር ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ ለመቀነስ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለማሳካት የሚረዳ ዘላቂና ሰላማዊ የመንገድ ትራንስፖርት ስርአት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሸከሪካሪዎች ቁጥር እንዲበራከትና ሞተር አልባ ትራንስፖርት በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

በከተሞች የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ማስፋፋት የአየር ብክለትን ለመቀነስ ከፍተኛ እገዛ ስላለው ቁጥራቸውን ከፍ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተሸከርካሪዎችን የአገልግሎት ዘመን የሚገደብ አዲስ መለኪያ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ፀድቆ ወደ ተግባር ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።፡

አሽከርካሪዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ባህላቸውን በማሳደግ የአየር ብክለትን በመቀነስ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በአገራችን የተሸከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ለአገር ኢኮኖሚና ማህባራዊ ፋይደው የጎላ ቢሆንም በአግባቡና በጥንቃቄ ካልተጠቀምንበት አደጋው የከፋ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በአፍሪካ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የተሽከርካሪዎች ጭስ፣ የአካባቢ መራቆት እንዲሁም ከኤሌክትሪክ ይልቅ በማገዶ እንጨት ምግባቸውን የሚያበስሉ ሰዎች ቁጥር በመበራከቱ የአየር ብክለት እየተባባሰ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም