በህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለማዳን በጋራ ቆመዋል - ኢዜአ አማርኛ
በህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለማዳን በጋራ ቆመዋል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ) በህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለማዳን በጋራ መቆማቸውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደማቸውን ለግሰዋል።
የቡድኑ ሰብሳቢ የቀድሞው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝደንት ደራሲ ጌታቸው በለጠ፤ አሁን ያለንበት ጊዜ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና በጋራ የቆሙበት ነው ብለዋል።
የአሀዱ ቴሌቭዥን እና ራድዮ ስራ አስኪያጅ እና የቡድኑ አባል አቶ ጥበቡ በለጠ፤ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን ሲያስተዳደር የነበረው ህወሃት በዘርና በጎሳ ከፋፍሎ በጥላቻ ትርክት አገሪቱን ሲያተራምስ መቆየቱን ተናግሯል።
ከለውጡ በኋላ ግን ሁሉም ዜጋ በአንድነትና ወኔ በመታጠቅ የታላቋን ኢትዮጵያ ክብር ለመመለስ መሰለፋን ተናግረዋል።
ይህ አንድነት ተጠናክሮ ከቀጠለ ወራሪውን ህወሃት ብቻ ሳይሆን ድንበር አልፎ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚዳፈር ወራሪ ኃይል ጠራርጎ ለማስወጣት ያስችላል ብለዋል።
ሞዴል እና የቱሪዝም አስተዋዋቂ እንዲሁም የቡድኑ አባል ወይዘሮ ፈትያ መሀመድ፤ ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚድያዎች የሚለቀቁ መረጃዎችን በመመልከት ሊረበሽ አይገባም ብላለች።
በተለይም በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የህልውና ዘመቻውን አቅማቸው በፈቀደው መልኩ በተለያየ መንገድ ሊደግፉ ይገባል ነው ያለችው።