በማይጨውና አላማጣ ከተሞች በ146 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በማይጨውና አላማጣ ከተሞች በ146 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ ተባለ
ማይጨው ነሀሴ 6/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨውና አላማጣ ከተሞች በተያዘው የበጀት ዓመት በ146 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተገለጸ፡፡ የከተሞቹ አስተዳደሮች እንዳሉት የልማት ፕሮጀክቶቹ በ2011 በጀት ዓመት የሚከናወኑ ሲሆን ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችንም የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡ የማይጨው ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አታኽልቲ ፀጋይ እንደገለጹት በአስተዳደሩ ከሚከናወኑ የልማት ሥራዎች መካከል 6 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ፣ 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድና ሰባት ኪሎ ሜትር የጎርፍ መቀልበሻ ቦይ እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡ የልማት ፕሮጀክቶቹን ለማከናወን በአስተዳደሩ 47 ሚሊዮን ብር በጀት የተመደበ ሲሆን ሕብረተሰቡም በጉልበት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ወደ ከተማው የሚመጣውን ጎርፍ ከመግታት በተጨማሪ የከተማ መንገድ ተደራሽነት እንደሚያሰፉም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ በአዲሱ የከተማው የእድገት ፕላን መሰረት ወደ ከተማው በተካለሉ ሦስት የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ መብራትና የመጠጥ ውሃ ማስፋፋት ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡ የመንግስት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለመስጠት እንዲቻልም በ24 ሚሊዮን ብር የአገልግሎት መስጫ ህንጻ እንደሚገነባም አቶ አታኽልቲ ተናግረዋል፡፡ የህንጻው መገንባት ተበታትነው አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ወደ አንድ ከማምጣት ባለፈ ለቤት ኪራይ ይወጣ የነበረውን ወጪ እንደሚያስቀረው ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የ13 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍና የጠጠር መንገድ ግንባታ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዝመራ አድሃና ናቸው፡፡ ከመንገዱ በተጨማሪ የ6 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መቀልበሻ ካናልና የአቃፊ ግንቦች ግንባታ ሥራ የፕሮጀክቱ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ምክትል ክንቲባዋ ገለጻ ወጣቶችን የመረጃ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲቻል የኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ማዕከል ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች መንግስት 75 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡንም ወይዘሮ አዝመራ አመልክተዋል፡፡ እንደኃላፊዎቹ ገለጻ በሁለቱም ከተሞች በሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶች ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶችን በሥራ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶችን በማህበር የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ኃላፊዎቹ አያይዘው ገልፀዋል፡፡