የሽብር ቡድኑን የጥፋት አጀንዳ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቅጡ እየተረዳው ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሽብር ቡድኑን የጥፋት አጀንዳ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቅጡ እየተረዳው ነው
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአሸባሪውን የሕወሃት ቡድን የጥፋት አጀንዳ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቅጡ እየተረዳው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ የአሸባሪውን ሕወሃት ቡድን ወንጀሎች መንግስት በተደጋጋሚ ይፋ ቢያደርግም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሳይረዳው ቆይቷል ብለዋል።
ከሰሞኑም የአሜሪካውን ረድኤት ድርጅት/ዩ ኤስ አይ ዲ/ እና መሰሎቹ የአሸባሪ ቡድኑን እኩይ ተግባር በመኮነን ያወጡት መግለጫ መንግስት ሲገልጻቸው ከነበሩት የቡድኑ ወንጀሎች የተለየ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሽብር ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በሂደትም ቢሆን እየተረዳ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘግይቶም ቢሆን የሽብር ቡድኑን የጥፋት አጀንዳ በመረዳቱ የኢትዮጵያ መንግስት በአድናቆት ይመለከተዋል ብለዋል አምባሳደር ዲና።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦቱን እንደሚያጠናክር ገልጸው፤ መንግስትን በእርዳታ ማስተጓጎል መኮነንም ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና ሱዳንን ግንኙነት በተመለከተም ኢትዮጵያ አሁንም የድንበር ጉዳይ በሶስተኛ ወገን አደራዳሪነት ሳይሆን በሁለቱ አገሮች ቀደምት የጋራ መርሆ ስምምነት እንዲፈታ ትሻለች ብለዋል።
በዜጋ ዲፕሎማሲ ረገድ ባሳለፍነው ሳምንት ከሳዑዲ አረቢያ፣ የመንና ታንዛኒያ ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ጠቅሰዋል።
መንግሰት ለዜጎች መብትና ክብር ትኩረት ይሰጣል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ በተለይም በሳኡዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት ኤምባሲዎቿን እየዘጋች ነው" የሚባለውም በተቋማዊ ማሻሻያ መሰረት ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ አቅም ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የሚዘጉ ኤምባሲዎችን በየአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮው እንደማይስተጓጎልና ይልቁንም 'ላፕቶፕ አምባሳደር' በተሰኘው የዲፕሎማሲ ስልት ጉዳዮች ከአዲስ አበባ በተቀመጡ አምባሳደሮች ይከወናል ብለዋል።