ቀጥታ፡

በሰሜን ወሎ ዞን ራያና ቆቦ ወረዳዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ተገቢው ድጋፍ አልተደረገልንም አሉ

ወልድያ ነሀሴ 6/2010 ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ራያና ቆቦ ወረዳዎች የሚገኙ ወገኖች ተገቢው ድጋፍ  አልተደረገልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገለፁ፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ሶስት ዞኖች ከ10 ወራት በፊት የተፈናቀሉት እነዚሁ ወገኖች ቅሬታቸውን የገለፁት ትናንት በቆቦ ከተማ ቀይ መስቀልና የሃይማኖት ተቋማት ያሰባሰቡትን የአልባሳትና የገንዘብ ስጦታ ባከፋፈሉበት ወቅት ነው፡፡ ከደምቢ ዶሎ ዞን ከነቤተሰሳባቸው የመጡትና የተፈናቃይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክፍሉ ከበደ በሰጡት አስተያየት ባለፈው ጥቅምት 2010 ቤት ንብረታቸውን ጥለው በመምጣት ከዘመድ ተጠግተው በመኖር ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ በቆይታቸውም መንግስት አንድ ጊዜ ብቻ 45 ኪሎ ስንዴ በአባወራ ከመስጠቱ በቀር ምንም አይነት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው አስረድተዋል፡፡ ‘‘አሁን የተፈናቃዩ አንገብጋቢ ችግር መጠለያና የእለት ምግብ ማጣት በመሆኑ የዞኑ አስተዳድር ችግሩን ሊፈታልን ይገባል'' ብለዋል። ‘‘በተለይ በገጠር ለሚኖረው ተፈናቃይ የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት የቀበሌና የወረዳ አመራሮች ከክልል መመሪያ ካልመጣ በማለት እያጉላሉን እንገኛለን'' ብለዋል። ከቄለም ወለጋ የመጡት አቶ መሰለ ዝናቤ በበኩላቸው ‘‘ለ10 ወር የተሸከመን ቤተሰብ አሁን ላይ እየተሰላቸ ስለመጣ መንግስት ቤት የምንሰራበት ቦታ ሰጥቶን ራሳችን ልንችል ይገባል'' ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አንዳንድ ተቋማት በተለይ ደግሞ የቆቦ ከተማ ወጣቶች በየጊዜው ከሕዝቡ ገንዘብና ምግብ እያሰባሰቡ ሲደግፏቸው መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ዞን የመጡት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ደስየ ውቡ እንደገለፁት ደግሞ ከ30 ዓመት በላይ ከኖሩበት አካባቢ ሃብት ንብረታቸውን ጥለው የመጡ በመሆኑ የአካባቢያቸው አስተዳድር ቦታ በመስጠት እንዲያቋቁማቸው ጠይቀዋል። ወይዘሮ በላይነሽ ዘለቀ በበኩላቸው ‘‘በቀበሌ ተመዝግበው እንደማንኛውም ነዋሪ ዘይትና ስኳር ማግኘት አልቻልንም፣ ልጆቻችንም ‘መሸኛ አላመጡም' በሚል የመማር እድል ተነፍጓቸዋል'' ብለዋል፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ የሀብት ልማት ኃላፊ አቶ መንገሻ አበበ በእለቱ ለ50 አቅመ ደካማ ሴቶች ለእያንዳንዳቸው 500 ብርና አልባሳት ሰጥተዋል። ለሌሎች ተፈናቃዮች ደግሞ አልባሳትና የቤት ቁሳቁስ ድጋፍ መከፋፈሉን ተናግረዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ደምሌ መንግስቱ እንደገለጹት ሁለት ሺህ ለሚደርሱ ተፈናቃዮች የሶስት ወር ቀለብ የሚሆን በነፍስ ወከፍ 45 ኪሎ ስንዴ መከፋፈሉን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ አካላትና የከተማው ወጣቶች የገንዘብና የአልባሳት ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ገልጸዋል፡፡ ‘‘ተጨማሪ የምግብ እርዳታ እንዲደረግላቸው የቁጥራቸው መረጃ ለሚመለከተው አካል በማስተላለፍ እየተጠባበቅን እንገኛለን'' ብለዋል። ተፈናቃዮች ከቄለም ወለጋ፣ ከደምቢዶሎና ከቡኖ በደሌ አካባቢ የመጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም