የአሸባሪው ወረራ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት እንዲነሱ ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪው ወረራ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት እንዲነሱ ያደረገ ነው
ጎንደር፤ ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ) ''የህወሃት የሽብር ቡድን ወረራና ጥቃት ኢትዮጵያውያንን ለህልውና ዘመቻው ከዳር እስከ ዳር በጋራ እንዲነሱ ያደረገ ነው'' ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ር አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
''የአማራና የቅማንት ህዝቦች ዘመናትን ያስቆጠረ ወንድማማችነት በጽንፈኞችና በጸረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች አይበረዝም" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በጎንደር ከተማ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
ቡድኑ ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያዊያንን ለመለያየትና ለመከፋፈል የሸረበው ሴራ በህልውና ዘመቻው ሊከሽፍ መቻሉን ገልጸዋል።
የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓላማ የተረዱ ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በስፋት በመንቀሳቀስና በአንድነት በመቆም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣውን ሃይል በጋራ መክተው በመመለስ አኩሪ ጀግንነት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጎንደርና አካባቢው ህዝብ በግንባር ለተሰለፈው ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ደጀንነቱን ከማረጋገጥ ባለፈ ዘምቶ በመፋለም ያሳየው ጀግንነት ታላቅ ክብር የሚያሰጠው ነው ብለዋል፡፡
''በጦርነቱ ወገን ብዙ ድሎችን እያስመዘገበ ይገኛል'' ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ቀሪ ስራዎችን በማከናወን የሽብር ቡድኑ የወረራቸውን አካባቢዎች ነጻ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የቅማንትና አማራ ህዝቦችን የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች በመናድ የሽብር ቡድኑ ከፋፋይ ተልእኮ አስፈጻሚ በመሆን የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ህዝቡ በጋራ ሊታገላቸው እንደሚገባ አፈ ጉባኤው አደም ፋራህ አሳስበዋል።
መንግስት ከሀገር ሽማግሌዎችና ሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን የጀመረውን የሰላም ጥረትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በመድረኩ የሃገር ሽማግሌዎችን የሰላም ጥረቶች ሪፖርት ያቀረቡት አቶ አራጋው ገበየሁ፤ የቅማንት ህዝቦች ከአማራው ወገናቸው ጎን በመቆም በህልውና ዘመቻው በጋራ ለመዋደቅ ዝግጁነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ብለዋል።
የቅማንት ህዝብ የሰላም አየር የናፈቀው ነገር ግን እራሳቸውን ነጻ ያላወጡ ነጻ እናወጣሃለን በሚል የሕወሃት ተላላኪ በመሆን ህዝቡን የሚያሰቃዩ ሃይሎችን ህዝቡ በጋራ መታገል ይኖርበታል ሲሉ አመልክተዋል፡፡
ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ አደም መሃመድ በበኩላቸው፤ ''የሁለቱ ህዝቦች ዘመናትን የዘለቀው የአብሮነት እሴቶች በሴረኞችና ከፋፋዮች የሽብር ተግባር ሊሸረሸር አይገባውም'' ብለዋል፡፡
የህወሃት የሽብር ቡድን ተላላኪ በመሆን የእነሱን ተልእኮ ለማስፈጸም በሚደረግላቸው የገንዝብ ድጋፍ ሁለቱን ህዝቦች ለማጋጨት የሚጥሩ ሃይሎችን ህዝቡ አጥብቆ ሊታገላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ህወሃት በስልጣን ዘመኑ የቅማንትን ህዝብ ማንነት በመካድ በህዝብና ቤት ቆጠራ ጭምር እንዳይታቀፍ ያደረገ መሰሪ ድርጅት መሆኑን ጠቁመው፤ የሱ ተላላኪ የሆኑ ሃይሎች በቅማንት ህዝብ ላይ የታሪክ ክህደት የፈጸሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግስት የጀመረው የሰላም ጥረት እንዲሳካ ህዝቡ ከሀገር ሽማግሌዎችና ሃይማኖት አባቶች ጎን ሊቆም ይገባል'' ያሉት ደግሞ የሃገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አዳነ አዳምሰገድ ናቸው፡፡
በቅማንትና አማራ ስም የሚነግዱ ቡድኖችን ህዝቡ አጋልጦ ለህግ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ከቅማንት ኮሚቴ ጋር የተጀመረው በጎ ውይይትና ድርድር በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።
በምክክር መድረኩ ከጎንደር ከተማና አካባቢው የተውጣጡ የቅማንትና አማራ ተወላጆችን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከፌደራል ክልል ዞንና ወረዳ የመጡ ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸውን ታውቋል፡፡