ኢትዮጵያዊያን የአገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ጠላትን በጋራ መመከት አለብን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን የአገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ጠላትን በጋራ መመከት አለብን
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን የአገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ጠላትን በጋራ መመከት ይጠበቅብናል ሲል አትሌት ገዛኸኝ አበራ ተናገረ።
በአርሲ ዞን ሎዴ ሄጦሳ ወረዳ የተወለደው የ43 ዓመቱ አትሌት ገዛኽኝ አበራ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር መሳተፍ የጀመረው እ.አ.አ አቆጣጠር 1999 ነው።
አትሌቱ በማራቶን ውድድር ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ወክሎ ተሳትፏል።
አትሌት ገዛኸኝ ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ የገዘፈ ልዕልና፣ ክብርና ጥልቅ ታሪክ ያላት ታላቅ አገር ናት ብሏል።
ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ መድረኮች መሳተፍ በተለይም በአትሌቲክስ አደባባይ ሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ ሲል በልጆቿ የሚፈጥረው ስሜት የተለየ ነው ሲል ገልጾታል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እየተውለበለበ በብሔራዊ መዝሙሯ ሲታጀብ ደስታ፣ ኩራቱና ክብሩ ይልቃል ይላል አትሌት ገዛኽኝ።
"አገር የእኔነት ስሜት ነው፤ ማንነታችን ነው፤ አገር ከሌለች ሁላችንም የለንም፤ አገር ስትኖር ነው መነጋገርም ሆነ መወያየት የሚቻለው" ብሏል።
"የጥልቅ ታሪክ ባለቤቷ ኢትዮጵያ የሚኮሩባትና በጎ ችሮታ የተሰጣት በመሆኗ ኢትዮጵያዊ ሆነን ያገኘነው ከመብዛቱ ውጭ ያጣነው ነገር የለም" ብሏል አትሌት ገዛኸኝ።
እናም የዚህችን ድንቅ አገር ህልውና ለማስጠበቅ ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ልዩነት በጋራ መቆም አለብን ብሏል።
አትሌት ገዛኸኝ "ሊነጋ ሲል ይጨለማል" እንደሚለው ብሂል ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ችግር ተሻግራ ከፍ የምትልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም" ሲል እምነቱን ገልጿል።
ለዚህም ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን በማጥበቅ በጀግኖች አባቶቻችን መስዋዕትነት የተረከብናትን አገር ማስቀጠል ይጠበቅብናል ብሏል።
በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚቃጣውን ማንኛውንም ትንኮሳ በጋራ እንመክታለን ሲልም አክሏል።
አትሌት ገዛኽኝ እ.አ.አ 2000 በሲድኒ በተካሄደው 27ኛው የኦሊምፒክ ውድድር፤ እንዲሁም እ.አ.አ በ2001 በኤድመንተን 8ኛው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።