በሐረሪ ክልል የኮሮናን ቫይረስ ለመከላከል መዘናጋት በመኖሩ ስርጭቱ እየጨመረ ነው

ሐረር፤ ነሐሴ 27/2013(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስን በመከላከሉ በኩል መዘናጋት በመኖሩ ስርጭቱ እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም አስታወቁ፡፡
ቢሮው ዓመታዊ የሥራ ግምገማውን ከባለድርሻ አካላት ጋር በሐረር ባካሄደበት ወቅት ሃላፊው እንደተናገሩት፤ በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ቢመዘገብም አሁን የሚታየው መዘናጋት ግን አሳሳቢ ነው፡፡

በክልሉ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ ስምንት በመቶ፤ የሞት ደግሞ አራት በመቶ መድረሱንም በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የወረዳ አመራሮች የሕዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ ትኩረት እንዲሰጡ ሃላፊው አሳስበዋል።

ለሕዝቡ የሚሰጠው አገልግሎትም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አጠቃቀምን መሰረት ያደረገ መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል።

በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ቱፋ በበኩላቸው፤  በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ በክልሉ በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በተያዘው  ወር መጀመሪያ ሳምንት 1 ነጥብ 1 የነበረው የቫይረሱ ስርጭት በተያዘው አራተኛው ሳምንት ወደ 10 ነጥብ 1 ማሻቀቡን አመላክተዋል፡፡

ህብረተሰቡ የቫይረሱ መከላከያ ጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 58ሺህ 933 ሰዎች መካከል 4ሺህ 404 ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና የ178 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ከጤና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም