ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና እንዲረጋገጥ የኬንያ ፍላጎት ነው... የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይቼል ኦማሮ

ነሐሴ 27/2013 (ኢዜአ) "ኬንያ የምትፈልገው የኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና እውን ሲሆን ማየት ነው" ሲሉ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይቼል ኦማሮ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኬንያ አቻቸው ራይቼል ኦማሞ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይቼል ኦማሞ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኬንያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይት በወቅታዊ ሁኔታዎች በተለይም በትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ መክረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በእነዚህና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ለሚኒስትሯ ገለጻ እንዳደረጉላቸው ውይይቱን የተከታተሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።

ኬንያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ላሳየችው አጋርነትም ምስጋና አቅርበዋል ብለዋል።

የኬንያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ራቼል ኦማሞ በውይይቱ ወቅት የአገራቸው ፍላጎት የኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግና እውን ሲሆን ማየት ነው፤ ለዚህም ኬንያ ቁርጠኛ ናት ማለታቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም