ቀጥታ፡

በመላ ኢትዮጵያ በጳጉሜን አምስት ቀናት የሚካሄድ ፀሎትና ምህላ ታወጀ

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በመላ ኢትዮጵያ ከጳጉሜን 1 እስከ 5 ቀን 2013 የሚቆይ ልዩ የፀሎትና ምህላ መርሃ- ግብር አወጀ።

የፀሎትና ምህላ መርሃ-ግብሩ "የላቀ በጎነትና መልካምነት ለአገር ሠላም፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ-ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ወቅታዊውን አገራዊ ሁኔታና መጪውን አዲስ ዓመት አስመልክተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

እየተገባደደ ባለው ዓመት አገሪቷ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበች ቢሆንም በዚያው ልክ ሳንካዎች አጋጥመዋታል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በሠላም መጠናቀቁ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌትና ሌሎችም በስኬት መከናወናቸው የሕዝቡን ተስፋ ያለመለሙ ሁነቶች ናቸው።

በአንጻሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ ብሔርና ኃይማኖት ተኮር ግጭቶች በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት ካጋጠሙ ሳንካዎች ይጠቀሳሉ።

ጠቅላይ ፀሃፊው በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ሞት፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደምም አሉታዊና ፈታኝ ክስተቶች ሆነዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የዘለቀ የመከባበር፣ የሠላም፣ አብሮ የመኖር፣ ኃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመቻቻል የመፍታት ጽኑ መሰረት ያዳበረ እሴት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ይህን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጥንካሬ ለመሸርሸር የሚጣጣሩ ኃይሎች አገር ለማፍረስ ሲታትሩም ይስተዋላል ነው ያሉት።

እነዚህ ሃይሎች የኢትዮጵያን መለወጥና ማደግ ከማይሹ የውጭ ጣልቃገብ አገራት ጋር በማበር በሚፈጽሙት ተግባር በአገሪቷ ሠብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ማየት እየተለመደ መምጣቱንም አንስተዋል።

የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ጉባዔው 'ከፈጣሪ ጋር መጣመር፣ ፈጣሪን መለመንና ይቅርታ የመጠየቂያ ጊዜው አሁን ነው ብሎ ያምናል' ብለዋል።

በመሆኑም ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታውንና መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመላ አገሪቷ ከጳጉሜን 1 እስከ 5 ቀን 2013 ለአምስት ቀናት የሚቆይ የፀሎትና ምሕላ መርሃ-ግብር ታውጇል ሲሉ አስታውቀዋል።

መርሃ-ግብሩ አገሪቷና ሕዝቦቿን ያጋጠማቸውን ፈተና ለመሻገር ፈጣሪያቸውን የሚማጸኑበት፣ እርቅ እንዲወርድና ቀናነት እንዲጎላ ማድረግን ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሁሉም እምነት ተከታይ ዜጎች በእነዚህ ቀናት የዜጎች ሞት፣ አካል መጉደልና መፈናቀል እንዲያቆም በፍጹም ልባቸው ልመናቸውን ወደ ፈጣሪያቸው እንዲያሰሙም ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል።

በትግል ውስጥ ያሉ አካላትም ልባቸውን ለይቅርታ ከፍተው ትውልዱ ይቅር ባይነትና ለሠላም አጎንብሶ ማለፍን እንዲማሩ ዓርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በእነዚህ የመሸጋገሪያ ቀናት ልዩ የፀሎት መርሃ-ግብር አባቶች ምዕመኑ እንዲሳተፍ በማድረግና ቤተ-እምነቶች በማንኛውም ሠዓት ክፍት ሆነው እንዲፀለይባቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋልም ተብሏል።

የፀሎትና ምህላ መርሃ-ግብሩ "የላቀ በጎነትና መልካምነት ለአገር ሠላም፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄድ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም