ቀጥታ፡

አሸባሪውን ህወሓት በመደምሰስ የአገር ሉዓላዊነትንና አንድነትን እናስጠብቃለን

ነሐሴ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪውን ህወሓት በመደምሰስ የአገር ሉዓላዊነትንና አንድነትን እንደሚያስጠብቁ በማይፀብሪ ግንባሪ የተሰማሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ገለፁ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሠራዊቱ አባላት አሸባሪውን ህወሃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት እንደሚያስከብሩ ተናግረዋል።

 በየግንባሩ አኩሪ ድል እየፈፀሙ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት የኢትዮጵያን ሕዝብ አደራ ተቀብለው አሸባሪውን የህዋሓት ቡድን ወደ መቃብር እየከተቱት እንደሚገኙም ገልፀዋል።

"ኢትዮጵያ የጀመረችው የልማት ጉዞ እንዳይደናቀፍ መስዋዕት በመሆን አሸባሪውን ቡድን እየደመሰስን እንገኛለን" ብለዋል።

ቡድኑ በአሁኑ ወቅት አቅሙ ተሟጦ የመዋጋት ጉልበቱ በማለቁ የሕዝብ ንብረት መዝረፍና ማውደም ተግባር ላይ እንደተሰማራ ጠቁመዋል።

"አሸባሪው ህወሃት ጦርነት የከፈተው ከግለሰብ ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነው፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መጋጨት ደግሞ ኪሳራው የከፋ ነው" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ታሸንፋለች" በሚል መሪ ሃሳብ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ከኦሮሚያ ሚሊሻ ጋር በመሆን በአሸባሪው ቡድን ላይ ከፍተኛ ቁሳዊና ሠብዓዊ ኪሳራ እያደረሱ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው በመሆን እያደረገ ያለው ድጋፍ እውነተኛ የሕዝብ ልጆች መሆናቸውን ያረጋገጠ ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል።

በመጪው አዲስ ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የሆነው አሸባሪው ህወሓት እንደሚደመሰስ ገልጸው፤ መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት የሆነውን ድህነት ለመደምሰስ ሠራዊቱ ወደ ልማትና ብልፅግና የሚጓዝበት እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም