የኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዓለም ዓቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል
ነሐሴ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታ ገለጹ።
ኢትዮጵያ፣ ኮሪያና ኢንዶኔዥያ በጋራ ያዘጋጁት በዓለም ዓቀፍ የሠላም ማስከበር ተግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና በበይነ መረብ መካሄድ ጀምሯል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ስልጠና እስካሁን በሠላም ማስከበር ሂደቱ የተገኙ ተሞክሮዎችና ያጋጠሙ ችግሮች ይዳሰሳሉ።
ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ የሠላም ማስከበር ሂደት ትልቅ ሚና እንዳላት የገለጹት ዶክተር ቀነዓ፤ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም አገራት ሠላም በማስከበር ረገድ ጉልህ ሚና ስትወጣ መቆየቷን አውስተዋል።
በዚህ ሂደት ከ100 ሺህ በላይ ወታደሮች ማሰለፏን ጠቅሰው፤ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ለሠላም ያላትን ስፍራ እንደሚያመላክት ተናግረዋል።
ዶክተር ቀነዓ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ይህንኑ ተግባር በብቃት ስትወጣ የቆየች እንደሆነችም አክለዋል።
ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያ ለሰላም ቅድሚያ ትሰጣለች፣ በዚህ መርህ የቀጣናውን ሰላም ማስከበር የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው" ብለዋል።
በቀጣይም ይህ የኢትዮጵያ ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በርዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና ኮሪያ ሰላም ማስከበሯ ይታወቃል።