የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየው ድጋፍ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየው ድጋፍ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖታል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/213(ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀብት አሰባሰብ ሂደት ያሳየው ድጋፍ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆኖታል" ሲሉ የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታ ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ለሰራዊቱ የተደረገውን ሀብት ማስባሰብ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም እስካሁን ባለው ሂደት ለመከላከያ ሠራዊቱ ሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 42 ሚሊዮን ብር ከዲያስፖራው መገኘቱን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 6 ሺ 679 ሠንጋዎች፣ ከ10 ሺ በላይ በግና ፍየል፣ በርካታ ብር ግምት ያለው ደረቅ ሬሽን ለሠራዊቱ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግስት፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ የንግድ ማህበረሰቡ እና ሌሎች ተቋማት አሁንም ለሠራዊቱ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ህልውና መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርቧል።
ብሔራዊ የሃብት አሰባሰቡ እስካሁን ከታሰበው በላይ በተሳካ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ አንድነት ጎልቶ የታየበት፣ ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ የተረጋገጠበት ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም በርካታ ወጣቶች ለአገር ህልውናና አንድነት መከበር መከላከያ ሠራዊትን እየተቀላቀሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተገደበ የደጀንነት ድጋፍ ለሰራዊቱ ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሆነለትም ዶክተር ቀነዓ አስረድተዋል።
በተለይ ደግሞ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል በ6800 አጭር የስልክ መልዕክት ሁሉም ሰው በድጋፉ እንዲሳተፍ የተደረገበት መንገድ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሸባሪው ሕወሃት እስኪወገድ ድረስ የሕዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።