ቀጥታ፡

አገር በቀል ሲቪክ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ በማሳየት ስሟን የሚያጠለሹ ምዕራባዊያን ድርጅቶችን ማጋለጥ አለባቸው

ነሀሴ 26/2013 (ኢዜአ) አገር በቀል የሲቪክ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ በማሳየት የምዕራባዊያን ድርጅቶችን ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ሊያጋልጡ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተናገሩ።

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት በተሰኘ አገር በቀል የሲቪክ ድርጅት አዘጋጅነት በሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የሕግ ማዕቀፍ አወጣጥ ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ቆይታ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ጉባዔ-ኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ እንደገለጹት አሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ የሲቪክ ማህበራትን ከፍተኛ ሃላፊነት የሚጠይቅ ነው።

ኢትዮጵያ በውጭ ሃይሎች በተለይም በምዕራባዊያን ጫና እየተደረገባት መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ መሃል አገር በቀል ተቋማት ከአገርና ከወገን ጎን በመቆም ሃላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢሰመጉ አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ንጹሃን ከሞት እስከ መፈናቀል የጉዳት ሰለባ መሆናቸውን በማውገዝ ከሰሞኑ ዝርዝር መግለጫ መውጣቱን አስታውሰዋል።

የአሸባሪው ቡድን ጥቃት በዓለም አቀፍ ሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም አካባቢው ሲረጋጋ መርማሪ ቡድን በመላክ ለሕዝብና ለዓለም አቀፉ  ማህበረሰብ መረጃዎች ይፋ ያደርጋል ብለዋል።

ኢሰመጉ ለሠብዓዊ መብትና ሕግ መከበር የቆመ ተቋም ነው ያሉት አቶ ዳን በቀጣይም ከተጎዱ ወገኖች ጎን በመቆም በንጹሃን ላይ ጥቃት ያደረሱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ አስፈላጊውን መረጃ አሰባስቦ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የሲቪክ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ችግር አንጻር ከሚዲያ ጋር በመቀናጀት ጠንካራ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የረድኤት ደርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታ ሲለግሱ ትክክለኛ ሰብዓዊ ተልዕኳቸውን ብቻ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በአንጻሩ አንዳንድ የውጭ ረድኤት ድርጅቶን ተከትሎ የሚሰማውን ቅሬታ እየተከታታለ መሆኑን ገልፀው፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ አላስፈላጊ ጫናና መካረር ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል።

በመሆኑም ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ ሚዛናዊና አንዱን ወገን ጫና ውስጥ የማይከት ይልቁንም የውጭ ረድኤት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር በተቃኘ አግባብ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበራት ህብረት ዋና ዳይሬክተርና የሲቪክ ሶሳይቲ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ንጉሱ ለገሠ ሲቪክ ማህበራት ስራቸውን በገለልተኝነት ማከናወን አለባቸው ይላሉ።

በወቅቱ የምዕራብ አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ጫና ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሆነ ይናገራሉ።

ድርጅታቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ አደረጃጀቶችን በበይነ መረብ ስብሰባ የኢትዮጵያን ችግር በኢትዮጵያ መፍታት እንደሚችሉና ጣልቃ ገብነት ችግሩን ይበልጥ እያባበሰው መሆኑን እያስረዳ ነው ብለዋል።

የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብትነት ለአሸባሪው ቡድን የልብ ልብ እየሰጠ አጎራባች ክልሎችን በመውረር ሌላ ጥፋት እንዲያደረስ እያደረገ በመሆኑ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀናል ብለዋል።

የጥቁር ነጻነት ቀንዲል የሆነችው ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ ስትወረር ጥቁር አሜሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው ለነጻነቷ መሟገታቸውን በማውሳት፣ ዛሬ ግን በተቃራኒው አፍሪካዊ አሜሪካን ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማድረጋቸው ከምን የመነጨ ነው በሚል ጠይቀናል ነው ያሉት።

በትናንትናው ዕለት ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ሃላፊ ጋር መወያያታቸውን የገለጹት ዶክተር ንጉሡ፤ በመጪው መስከረም ኢትዮጵያ መጥተው መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚመለከቱ የውጭ ሲቪክ ድርጅት አመራሮች እንዳሉ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የምዕራቡ ዓለም ጫና ከተነሳ ጉዳዩን በኢትዮጵያ ያጋመጠውን ችግር መፍታት ስለሚቻል ዕጃቸውን እንዲሰበስቡ ግፊት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተማጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሃይለማርያም በበኩላችው ሲቪክ ድርጅትች ሰላም እንዲሰፍን፣ ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና የሕግ ተጠያቂነት እንዲኖር ሚናችው ጉልህ ነው ብለዋል።

በአሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታም ሲቪክ ማህበረስብ ደርጅቶች ትልቅ ስራ መስራት እንደሚገባቸው ገልፀው፤ በተለይም አገሪቷ ወደ መረጋጋትና ልማት እንድትመለስ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን አክለዋል።

የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አገሪቷ ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን መነሻ ያደርጋሉ ያሉት አቶ ያሬድ፤ ለጣልቃ ገብነት መንስኤ የሆኑ የውስጥ ጉዳዮችን በቅድሚያ አገር በቀል ድርጅቶች ሊቀርፉ ይገባል ነው ያሉት።

በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ለዕውነተኛ ዓላማ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዳሉ ሁሉ የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የራሳቸውን ፖለቲካ የሚሰሩ፣ ሃሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ፣ የአገሪቷን ገጽታ የሚያጠለሹም እንዳሉ ጠቁመዋል።

ይህን መከላከል የሚቻለው አገር ውስጥ ያሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ለቆሙለት የሰብዓዊ መብት፣ የፍትሕና የተጠያቂነት ዓላማ በመስራት የተበላሸውን የአገሪቷን ገጽታ በማረም ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም