ኢትዮጵያዊያን በጋራ ከቆምን ማንም ሊያሸንፈን አይችልም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በጋራ ከቆምን ማንም ሊያሸንፈን አይችልም
ነሀሴ 26/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን የአገር ህልውና ለማስጠበቅ በአንድነት ሲቆሙ ምንም ኃይል ሊያሸንፋቸው አይችልም ሲሉ ብርጋዴር ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ ተናገሩ፡፡
የቀድሞ ሠራዊት አባል ብርጋዴር ጄኔራል ካሣዬ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም ኢትዮጵያዊያን አገር መውደድን፣ በአገር ጉዳይ በጋራ መቆምንና ለአገር አንድነት መዋደቅን ከጀግኖች አባቶች የተማሩት ነው ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ከጀግኖች አባቶቹ በተማረው የአገር ፍቅር ስሜት ለአገሩ ህልውና መከበር እየተዋደቀ ለሚገኘው ሠራዊት ድጋፍ በማድረግና ከጎኑ በመሰለፍ እየገለጸ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
'ኢትዮጵያን በጋራ ከቆምን ማንም ሊያሸንፈን አይችልም' ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ ይህንንም በተግባር እያስመሰከርን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በውስጡ የሚሽሎኮሎኩ ባንዳዎችን መጠበቅ ይኖርበታል ያሉት ጄኔራል ካሣዬ አገራችንን ለማዳን በጋራ የምንቆምበት ወቅት አሁን ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወደ ስልጣን በመጣበት ጊዜ ለአገር ከመስራት ይልቅ በሌብነት ተግባር ተጠምዶ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
የሠራዊቱ አመራሮች ወደ መቀሌ ሲሄዱ የሚመራ የለም በሚል እሳቤ ጥቃት መሰንዘራቸውን ያስታወሱት ብርጋዴር ጄኔራሉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ግን ለጥቃታቸው ሳይንበረከክ በኢትዮጵያዊ ወኔ ግብዓተ መሬታቸውን በመፈጸም ላይ ነው ብለዋል፡፡
የቀድሞ ሠራዊት አባላትም በሁሉም ረገድ ከሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን ገልጸው ደጀን የሆነው ሕዝብም እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ሠራዊቱ በአገሩ ጉዳይ በአንድነት ግዳጁን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸው በአጭር ጊዜ ውስጥም ግዳጁን በአሸናፊነት እንደሚያጠናቅቅም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡