ቀጥታ፡

የሸኔ የሽብር ቡድን በኦሮሞ ስም የሚነግድ የኦሮሞ ጠላት የጥፋት ኃይል ነው - አባ ገዳ ሁንዴ በየነ

አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2013(ኢዜአ) "የሸኔ የሽብር ቡድን በኦሮሞ ስም የሚነግድ ትናንት ኦሮሞን ሲገድል ከነበረው የህወሃት የሸብር ቡድን ጋር ጋብቻ የፈጸመ የኦሮሞ ጠላት ነው" ሲሉ አባ ገዳ ሁንዴ በየነ ገለጹ።

የኦሮሞ ወጣት ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም የኢትዮጵያን ህልውና ማስጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለአገር የሚራራ አንጀት የሌለው፣ በእናቶች እንባ የሚደሰት፣ አገር ሰትደማ የሚረካ፣ የከሃዲዎች ስብስብ ነው።

የሽብር ቡድኑ በስልጣን በቆየባቸው ዓመታት ዜጎችን ለእልቂት፣ ሀገርን ለምጣኔ ሃብታዊ መሽመድመድ፣ ወንድማማች የሆኑ የኢትዮጵያን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እርስ በርስ ለማጋጨት ሴራ ዘርግቶ ሲሰራ መቆየቱ ደግሞ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።

የሽብር ቡድኑ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በታላቅ ክብርና ደስታ በሚከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ የፈጸመው የዜጎች እልቂት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ሽብርተኛው የህወሃት ቡድን ዜጎች ለመብታቸው አደባባይ ሲወጡ ምላሹ አፈ-ሙዝ፤ ሃሴቱ ደግሞ የህዝብ ዋይታ መሆኑም እንዲሁ።

አባ ገዳ ሁንዴ በየነ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት፤የወያኔ ስርዓት ለኦሮሞ ህዝብ ጠላት ብቻ ሳይሆን ገዳይ፣ አውዳሚ፣ አጥፊና ለትውልዱ የማይበጅ ነው።

በወቅቱ የነበረው ስርዓት በተለይ ለኦሮሞ ወጣት እጅግ አስከፊ እንደነበረም ነው ያስታወሱት።

ትላንት የኦሮሞን ህዝብ ሲጨፈጭፉ የነበሩት የሸኔና የወያኔ የሽብር ቡድኖች ዛሬ በጋራ እንደሚሰሩ ይፋ ማድረጋቸው አዲስ ጉዳይ አለመሆኑንና የሽብር ቡድኖቹ የኦሮሞ ህዝብ ጠላት መሆናቸውን ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የሸኔ የሽብር ቡድንም በኦሮሞ ስም የሚነግድ ትናንት ኦሮሞን ሲገድል ከነበረ ኃይል ጋር ጋብቻ የፈጸመ ለኦሮሞ የማይበጅ የጥፋት ኃይል መሆኑን አንስተዋል።

የኦሮሞ ወጣት መስዋእትነት የከፈለላትን ኢትዮጵያ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ለህልውናዋ መዋደቅ እንዳለበትም አባ ገዳ ሁንዴ በየነ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም