ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሠራተኞች ለህልውና ዘመቻው ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሠራተኞች ለህልውና ዘመቻው ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 26/2013(ኢዜአ) ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሠራተኞች ለህልውና ዘመቻው ከ4ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።
የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ ምሩቃንና አልሙናይ ማህበር አባላትም ለሀገር መከላከያ ሠራዊቱ 367 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።
ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጥላሁን ጸጋዬ የገንዘብ ድጋፉን ለመከላከያ ሚኒስቴር የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል አስረስ አያሌው አስረክበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ማህበሩ ከመደበኛ ስራው ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በተለይም አሸባሪው የህወሃት ቡድን የአገር ክህደትን ከፈጸመበት ግዜ ጀምሮ ማህበሩ ሠራተኞቹን በማስተባበር የገንዘብና የአይነት ድጋፍ እንዲሁም የደም ልገሳ መርሃ-ግብር በማካሄድ አጋርነቱን እያሳየ ይገኛል ነው ያሉት።
107 የማህበሩ ሠራተኞች የመከላከያ ሠራዊቱን መቀላቀላቸውን ጠቅሰው፤ ሠራዊቱን ለተቀላቀሉ ሠራተኞችም ሙሉ ደሞዛቸውና ጥቅማጥቅማቸው ሳይቋረጥ እየተከፈላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የማህበሩ ሠራተኞች የህልውና ዘመቻውን ለማገዝ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።
በፋይናንስ፣በሰው ኃይልና በደም ልገሳ የሚደረገው ድጋፍ የህልውና ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሐረር ጦር አካዳሚ ምሩቃንና አልሙናይ ማህበር አባላት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት 367 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።
የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ሻምበል በቀለ ጸጋዬ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት ከገንዘብ ድጋፉ ባሻገር ባላቸው ልምድ ሠራዊቱን በስልጠና ለማገዝ ዝገጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን የራሱን የጭቆና አገዛዝ ለማስቀጠል ሲል የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጦር አካዳሚም ሆነ በደርግ መንግስት ወቅት የነበሩ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ላይ ማግለል ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰዋል።
ማህበሩ ባወጣው ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ በሀገር ላይ የተቃጣውን ክህደት ለመመከት በሰሜን አሜሪካና በሀገር ውስጥ ያሉ የማህበሩ አባላት በእውቀታቸውና በአቅማቸው የመከላከያ ሠራዊቱን እንዲደግፉ ማህበሩ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች አስታውቋል።
የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ የማህበሩ አባላት ለሀገራቸው ማናቸውንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ማህበሩ በአቋም መግለጫው ያሳወቀው።
በመከላከያ ሚኒስቴር የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄነራል አስረስ አያሌው በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ለህልውና ዘመቻው የሚያደርጉትን ድጋፍ አድንቀዋል።
ዜጎች በገንዘብና አይነት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ለሀገራቸው የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በተግባር ያሳዩት ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ በከሃዲዎችና በወንበዴዎች እንደማትፈርስ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኮሜርሻል ኖሚኒስ በፋይናንሰ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞቹን ለሀገራቸው ባላቸው ፍቅር ግንባር እንዲዘምቱ ያበረታታበትና የደገፈበት ሁኔታ ለሁሉም ተቋማት አርኣያ እንደሆነም አንስተዋል።
የሐረር ጦር አካዳሚ ምሩቃንና አልሙናይ ማህበር አባላት ሀገራቸውን ለማገዝ በቅንነትና ታማኝነት እያከናወኑ ላሉት በጎ ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል።
በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሠራተኞች ከገንዘብ ድጋፉ ባሻገር ደም በመለገስ ለመከላከያ ሠራዊቱ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል።