ቀጥታ፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ስልጣን ላይ በነበረባቸው ጊዜያት የትግራይ ክልል ስለ ህወሓት ክፉ ታስባለህ ተብለህ ደብዛህ የሚጠፋበት ክልል ነው

ነሐሴ 26/2013(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት በትግራይ ክልል ህዝብ ላይ ሲያደርስ የነበረውን ግፍና ጭቆና አደባባይ ወጥቶ ለመቃወም ይቅርና “ስለ ህወሓት ክፉ ታስባለህ” ተብሎ የምትታሰርበትና ደብዛህ የሚጠፋበት ክልል እንደነበር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ የመቀለ ከተማ ከንቲባ አቶ አታክልቲ ኃ/ሥላሴ አስታወቁ።

አቶ አታክልቲ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት ከማንም በላይ በትግራይ ክልል ህዝብ ላይ ግፍና ጭቆና ሲያደርስ ነበር።

ህዝቡም የሚደርስበትን ግፍና ጭቆና አይደለም አደባባይ ወጥቶ ሊቃወም “ስለ ህወሓት ክፉ ታስባለህ” እየተባለ ጨለማ እስር ቤት ውስጥ እየተጣለ ደብዛው የሚጠፋበት ሁኔታ መኖሩንም ነው የገለጹት።

አሸባሪው ቡድን ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የትግራይን ህዝብ በአንድ ለአምስት በማደራጀት “እገሌ ምን ያስባል” እየተባለ ህብረተሰቡ እርስ በርሱ ከጀርባው እንዲጠራጠርና እንዲፈራራ በማድረግ ህዝቡ አንድ ሆኖ ቆሞ የሚደርስበትን ግፍና መከራ እንዳይቃወም ሲያደርግ እንደነበርም አስታውቀዋል።

በዚህም ህዝቡ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ተወጥሮ ተይዞ አይደለም አደባባይ ወጥቶ ሃሳቡን በነፃነት ሊገልጽ፤ ቃላትም ሳይተነፍስ በጥርጣሬ ብቻ ጨለማ እስር ቤት ውስጥ እየተጣለ አያሌ ወጣት ደብዛው መጥፋቱን ጠቁመዋል።

አሸባሪው ቡድን ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የትግራይ ህዝብ ከሌላው ክልል ህዝብ በባሰ ሃሳቡን በነፃናት እንዳይገልጽና አማራጭ ሃሳብ እንዳይቀርብለት አፈና ሲደረግበት ከመኖሩ ባለፈ አሁን ላይ ጁንታው ህዝቡን መያዣ አድርጎ እጅ ተወርች አስሮ በአገሪቱ ከመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ተቋዳሽ እንዳይሆን እየሠራ ነው።

ሕፃናትን ሳይቀር በጦርነት እየማገደ ህዝቡን በረሃብ እያሰቃየ ይገኛልም ብለዋል።

"የትግራይ ህዝብ ከውጥኑ ጦርነት የመግባት ፍላጎት አልነበረውም። በጥቂት ቤተሰቦች የሀብትና የስልጣን ጥማት ሲባል ነው በክልሉ ይህ ሁሉ ቀውስ እየደረሰ ያለው" የሚሉት አቶ አታክልቲ፤ ህዝቡ በአሸባሪው ህወሓት ታፍኖ ድምፁን በነፃነት የሚያሰማበት መድረክ ባለማግኘቱና ሃሳቡን በነፃነት የሚገልጽበት ዕድሎች ባለመፈጠራቸው ትናንትም ዛሬም መራራ መስዋዕትነት እየከፈለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል ህዝብን ባህልና ታሪክ በማይመጥን እና ከሰውነት ተራ በወረደ መንገድ በአሸባሪው ቡድን የዕምነት ቦታዎቹ መዘረፋቸውን ጠቁመው፤ የሃይማኖት አባቶችን ሳይቀር ከማሰርና ከማንገላታት በዘለለ እስከ ህይወት መስዋትነት እንዲከፍሉ ተደርጓልም ነው ያሉት።

ዕርዳታን በማስተባበራቸው፤ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ እንዲገነባ በመሥራታቸው፤ የህዝብና የመንግሥት አገልግሎት መልሶ እንዲጀመር በመሥራ ታቸው፤ የአካባቢው ጸጥታ እንዲጠበቅ በማገዛቸው፤ በጥቅሉ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ውግንናና እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ጁንታው አንገቱን ያስደፋውን ህብረተሰብ ለመካስና የተጣመመውን ለማቃናት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በተለያየ ደረጃ ሲያገለግሉ የነበሩ ከ55 በላይ አባላትን ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ የጭካኔ ጥግ፣ የህዝቡን ባህልና ክብሩን በማይገልጽ፣ ለመናገር በሚዘገንን ሁኔታ መገደላቸውን አስታውቀዋል።

የቡድኑ አመራሮች “እኛ ስልጣን ላይ ከሌለን፣ እኛ ካልመራን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን” እስከማለት የደረሰ ጭካኔ ያላቸው አረመኔዎች ናቸው የሚሉት አቶ አታክልቲ፤ እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያዊነት ብሎም በትግራዊነት ሊታሰቡና ሊጠሩ የሚገባቸው አይደሉም ይላሉ።

የትግራይ ክልል ህዝብ "እነዚህን ግፈኞች በቃኝ ማለት አለበት። ከዚህ በኋላ ለእነዚህ ግለሰቦች የስልጣንና የሀብት ጥያቄ ሊሞት የሚገባው የትግራይ ወጣት መኖር የለበትም" ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ እህት ወንድሞቹ ጋር በጋራ በመቆም የኢትዮጵያ ህልውናን፣ ሰላምንና መረጋጋትን ለማስጠበቅ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት እንዳለበት የገለጹት አቶአታክልቲ፤ ይህንንም በተግባር ለማረጋገጥ እንቅስቃሴዎች ተጀምሯል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም