ስትራቴጂካዊ አካባቢ በሆነው የአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ በአፍሪካ ለሚኖር ሰላምና እድገት አሜሪካ ለኢትዮጵያ አጋርነቷን ማሳየት አለባት - ኢዜአ አማርኛ
ስትራቴጂካዊ አካባቢ በሆነው የአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ በአፍሪካ ለሚኖር ሰላምና እድገት አሜሪካ ለኢትዮጵያ አጋርነቷን ማሳየት አለባት
ነሃሴ 26/2013 (ኢዜአ) ወሳኝ ስትራቴጂካዊ አካባቢ በሆነው የአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ አፍሪካ ውስጥ ለሚኖር ሰላምና እድገት ኢትዮጵያን በመደገፍ አሜሪካ አጋርነቷን ማሳየት እንደሚገባት የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአሜሪካ ቅርንጫፍ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአሜሪካ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ለአንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ደብዳቤ አስገብቷል።
በደብዳቤው አሁን በኢትዮጵያ ለሚታዩ ችግር ያለፉትን ሠላሣ አመታት ፓለቲካው ሂደት ማወቅ ያስፈልጋል ብሏል።
በነዚህ አመታት ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መንገዶች በመሐከላቸው ቅራኔና መለያየት እንዲፈጠር መሠራቱን አመልክቷል።
አሸባሪው ሕወሓት ይመራው በነበረው መንግሥት መዋቅር ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የህዝብ ሀብት ዝርፊያ እና በመንግስታዊ የሽብር ወንጀሎች በተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣በጋዜጠኞችና በግለሰቦች ላይ ሲፈጸም ነበር ብሏል።
ህወሓት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ሰላማዊ መንገድን መምረጥ ትቶ ወደ ጦርነት መግባቱን አስታውሷል።
ባለፉት ሦስት አመታት የነበረ መዋቅሩን በመጠቀም ግጭቶች እንዲከሰቱ ዜጎች ለሞት እንዲዳረጉና በአገሪቱ ሰላም እንዳይሰፍን መሥራቱን ነው ደብዳቤው ያስገነዘበው።
ጥቅምት 24 /2013 ዓ.ም ደግሞ በአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የፌደራል መንግሥቱን በሀይል ከስልጣን የማስወገድ ሥራ ላይ መግባቱን አስታውቋል።
መንግስት ይህንን ተከትሎ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ መግባቱንና በመቀጠልም ለዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የእርሻ ስራዎች እንዲሰሩ የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውሶ አሸባሪዎች ህወሓት ግን ህጻናትን ለጦር በማሰለፍ ጭምር ወደ አጎራባች ክልሎች ጥቃት መሠንዘሩን አውስቷል።
በአፋርና በአማራ ክልሎችም ንጹሃን ላይ ጭፍጨፍ በማካሄድ ንብረት በማውደም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ማፈናቀሉን ነው ያመለከተው።
አሜሪካም በነዚህ ክልሎች የሚኖሩ ተፈናቃዮችን በመደገፍ አጋርነቷን እንድታሳይ ገልጾ ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ገለልተኛ በመሆን ድጋፏን እንድትሰጥ ጠይቋል።
በዮኔስኮ የተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶች ደህንነትና የህወሓት የውድመት አካሄድ እንደሚያሳስበውም አመልክቷል።
የአሜሪካ መንግስት በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነት በመረዳት ለአንድ ወገን ያደላ እይታውን እንዲያስተካክልና ይህንንም የሚያሰራጩ አለማቀፍ ሚዲያዎች እርምት እንዲሰጡ አሳስቧል።
ወሳኝ ስትራቴጂካዊ አካባቢ በሆነው የአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ አፍሪካ ውስጥ ለሚኖር ሰላምና እድገት ኢትዮጵያን መደገፍ የውዴታ ግዴታ መሆኑንና አሜሪካም ለዚህ አጋርነቷን እንድታሳይ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት የአሜሪካ ፍላጐት መሆኑንም እንረዳለን ብሏል ደብዳቤው።
በአሜሪካ የምንገኝ የሐይማኖት ተቋማትም የአሜሪካ መንግሥት የያዘውን አቋም እንዲፈትሽ፣ ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ ከማያደርገው ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ጫና አሜሪካ እጇን እንድታነሳ እንጠይቃለን በማለት ደብዳቤው ገልጿል።