ቀጥታ፡

በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ ሥርጭት ለመቀነስ "ቁጥብ የገንዘብ ፖሊሲ" ተግባራዊ ሊሆን ነው

ነሐሴ 25/2013 (ኢዜአ) በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ ሥርጭት ለመቀነስ "ቁጥብ የገንዘብ ፖሊሲ" ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ባንኩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የባንኮች መጠባበቂያና የብሔራዊ ባንክ የማዳበሪያ ወለድ ምጣኔን፣ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀምን፣ የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸውን ስለሚያሳውቁበት ሁኔታና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦንድን አስመልክቶ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አመላክቷል፡፡

የዋጋ ግሽበትን ለመግታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጫው አስፍሯል፡፡

ችግሩን ለመግታት አስፈላጊው የፖሊሲ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት ታምኗል።

በዚህም በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ ሥርጭት ለመቀነስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥብ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ወስኗል፡፡ 

እንደ ጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ከመስከረም 1 ቀን 2021 ጀምሮ ባንኮች ከሚሰበስቡት የተጣራ ቁጠባ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስቀምጡ ከሚገደዱት የመጠባበቂያ መጠን ከነበረው 5 በመቶ ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲል ተወስኗል ብሏል።

በተጨማረም ባንኮች ለአጭር ጊዜ የሚገጥማቸውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚበደሩበት ዓመታዊ ወለድ ምጣኔ ከ13 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ 

ቁጥብ የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃ እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ንረት ችግር ለመግታት አዎንታዊ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ በአንፃሩ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የጎላ አሉታዊ ተፅእኖ እንደማያስከትል ገልጿል፡፡

 የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ አኳያ በትኩረት መሥራት እንደተጠበቀ ሆኖ የተገኘውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ መጠቀም መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን አሳስቧል።

በባንኮች በኩል በሚገኝ የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም ላይ ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን ቀደም ሲል ባንኮች ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ ከዲያስፖራ ሂሳብና ከሌሎች ምንጮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያዝዘው መመሪያ ተሻሽሏል።

በዚህም ከወጪ ንግድ፣ ከግለሰብ ሃዋላና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ብቻ ከሚገኝ የውጭ ምንዛሪ 50 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ ተወስኗል።

ሌላው የውጭ ምንዛሪ ያስገኘ ማንኛውም የባንክ ደንበኛ ቀደም ሲል በውጭ ምንዛሪ ሂሳብ ውስጥ ያለጊዜ ገደብ መያዝ የሚችለው የውጭ ምንዛሪ መጠን ከ31 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 40 በመቶ ከፍ እንዲል ተወስኗል። ቀሪውን 10 በመቶ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ የሚጠቀሙት ይሆናል ተብሏል፡፡ 

እያንዳንዱ ባንክ ከዓመታዊ ጠቅላላ የብድር ክምችት አንድ በመቶ የልማት ባንክ ቦንድ እንዲገዛበት በቅርቡ የወጣው መመሪያ ያመለክታል።

የመድን ድርጅት ደግሞ  ከተጣራው ዓመታዊ ገቢያቸው ከ15 በመቶ ያላነሰ የልማት ባንክ ቦንድ እንዲገዙ ተወስኗል።

ቦንዱ መንግስት ዋስትና የሚሰጠውና በተነጻጻሪ የተሻለ ወለድ የሚከፈልበት ይሆናል።

ለሚወጡት መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ተፈፃሚነት የፋይናንስ ተቋማትና ደንበኞቻቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከተሰጠው ተልዕኮ አኳያ የኢኮኖሚውን ሁኔታ በየጊዜው እያየ ተጨማሪ የፖሊሲ እርምጃዎችን የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል።

ባንኩ ያወጣው የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸውን ስለሚያውቁበት ሁኔታና የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ቦንድን በሚመለከት ያወጣው ጨምሮ አጠቃላይ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም