ቀጥታ፡

ማህበሩ በአሸባሪው ህወሀት ወረራ ለተፈናቀሉ አንድ ሺህ አባወራዎች ድጋፍ አደረገ

ጎንደር ነሐሴ 25/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ-መስቀል ማህበር አሸባሪው ህወሀት በፈፀመው ወረራ ተፈናቅለው በደባርቅ ጊዚያዊ መጠለያ ለሚገኙ አንድ ሺህ አባወራዎች አልሚ ምግብና የቤት መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

በማህበሩ የጎንደር ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ አታለል ታረቀኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ በወረራው ከቤትና ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ የተደረገላቸው ከአዲ አርቃይ፣ ማይጸምሪና ዛሪማ አካባቢዎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያው ለሚገኙ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም  ለእናቶችና ህጻናት 338 ካርቶን ሃይል ሰጪ ብስኩት ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ ይገኝበታል፡፡

እንዲሁም ለቤት መገልገያ የሚያውሉት አንድ ሺህ የውሃ መቅጃ ጀሪካኖች፣ 2ሺህ ባልዲዎችና የልብስ ማጠቢያዎች ማከፋፋላቸውንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከአንድ ሺህ በላይ የግል ንጽህና መጠበቂያ ሳሙናዎች ተፋፍለዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ለተፈናቃዮቹ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶችን  እንዲሁም የብርድ ልብስና አንሶላዎች ለማከፋፈል መዘጋጀቱንም አቶ አታለል አስታውቀዋል፡፡

ማህበሩ ከአንድ ሳምንት በፊት በተመሳሳይ የአልባሳትና የአልሚ ምግብ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም