ቀጥታ፡

የመከላከያ ሠራዊቱ ጅግጅጋ ከተማ ከገባ ወዲህ ሰላማቸው መረጋገጡን ነዋሪዎች ገለጹ

ጅግጅጋ ነሃሴ 6/2010 በጅግጅጋ ከተማ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታትና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የችግሩ ሰለባዎች ገለፁ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ ጅግጅጋ ከተማ ከገባ ወዲህ ሰላማቸው መረጋገጡንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥና የነዋሪዎችን አብሮነት መመለስ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትናንት በጅግጅጋ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አስካለች ገብረመድህን "ቤታችን ሲዘረፍ ያስጣሉን ሶማሌ ወንድሞቻችን በመሆናቸው ችግር ፈጣሪ ወጣቶቹ እና ግብረአበሮቻቸው የሶማሌን ህዝብ አይወክሉም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ "በወቅቱ 14 ቤተሰቦቼን ሰብስቦ በቤቱ የደበቀን የሶማሊ ማህበረሰብ ህይወታችንን አትርፏል'' ያሉት ወይዘሮ ዓለም የቤታቸው ንብረት መዘረፉንና በአሁኑ ወቅት የሚለብሱት ሻሽ እንኳ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ''ለአምስት ቀናት በረሃብ ተጎድተናል ፤ መከላከያ ሰራዊቱ ደርሶልናል ሰላማችን በማግኘታችን ጉዳቱ አልተሰማንም። የተዘረፉ ንብረቶቻችን እንዲመለሱ እንፈልጋለን'' ያሉት ወይዘሮ ዓለም የሶማሌ ነዋሪዎች በብጥብጡ ተሳትፎ የነበራቸው ወጣቶችን በማጋለጥ  የጀመሩትን አጋርነት እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡ ከተጎጂዎች መካከል ሌላው አስተያየት ሰጭ ኢንጅነር ክፍሌ ይልማ በበኩላቸው በሁከቱ ለጉዳት ቢዳረጉም ችግሩ በቀጣይ እንዳይደገም ለዘመናት በሰላም እና በፍቅር አብሮ በኖረው ህብረተሰብ ዘንድ ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ውይይቱን ከክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሀምዲ አደን ጋር በመሆን የመሩት ሌተናል ጄነራል ሐሰን ኢብራሂም በበኩላቸው በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማሰብ መከላከያ ከልዩ ኃይል ጋር ሊዋጋ ነው በማለት ከእውነት የራቀ ወሬ በመንዛት ህዝቡ እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ ኃይሎችን ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ የፀጥታ ችግሩን ለማስተካከል የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ አባላት ለሚያደርጉት ጥረት ህዝቡ ከጎናቸው እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን መከላከያ ሰራዊቱና የማህበረሰቡ መሪዎች ለሚያደርጉት ጥረት ስኬታማነት የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ሊያግዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የክልሉ መገናኛ ብዙሃንም በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ዘገባዎችን እንዲሰራ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ የክልሉ ልዩ ሀይል የሰራቸው በርካታ መልካም ስራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ሌተናል ጄነራል ሐሰን የክልሉ ልዩ ኃይል አመራሮች ከህዝቡ ጋር በመመካከር የሚታዩ ችግሮችን ለማረም በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀምዲ አደን በበኩላቸው የኤፌድሪ መከላከያ ሠራዊቱና የክልሉ ልዩ ኃይል ለህዝቡ ጥቅም ለአንድ ዓለማ የቆሙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በጥፋት ኃይሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አቶ ሀምዲ በክልሉ መንግስትና በራሳቸው ስም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ንብረት የወደመባቸውን ወገኖች ለመካስና የተዘረፈውን ንብረት ለማስመለስ፣ እንዲሁም ተጎጂዎችን ለማቋቋም የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ወደሥራ መገባቱን ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም