ወራሪውን ጠላት በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅም ሀገራዊ ግዴታችን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወራሪውን ጠላት በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅም ሀገራዊ ግዴታችን ነው
ደሴ ነሐሃሴ 25/2013 (ኢዜአ) የውጭ ጫናን በጋራ በመቋቋምና ወራሪውን ጠላት በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ሀገራዊ ግዴታችን ነው ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ስብሰባ የተቀመጠው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የተንፀባረቁ ሀሳቦች የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን ድብቅ የጥፋት አጀንዳ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ሚናው የጎላ ነው፡፡
ሀገሪቱን ለማፍረስ የሚታትሩ ሀገራት ቢኖሩም በኢትዮጵያ ህዝብና ወዳጅ ሀገራት እየከሸፈ እንደሚገኝ ነው የተመለከተው።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ይመር አሊ፤ አሸባሪው ቡድን ገና ሲፈጠር ለውሸት፣ ለጥፋትና ኢትዮጵያ ለመበታተን መሆኑን ባሳለፍናቸው ጊዜያት መረዳት ችለናል ብለዋል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፡፡
በተለያዩ የዓለም ሀገራት ለመብታቸውና ለዓላማ የሚታገሉ ኃይሎች ቢኖሩም ህወሓት ግን በማወናበድ ብቻ እድሜውን ሊያራዝም ቢሞክርም ሊሳካለት እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተመሳጥሮ የዓለምን ህዝብ በሐሰት ወሬ ለማወናበድ ቢሞክርም እየከሸፈበት መሆኑን የፀጥታው ምክር ቤት ካካሄደው ስብሰባ መረዳት እንደማያዳግት ጠቅሰዋል።
በምክር ቤቱ የተንፀባረቁ ሀሳቦችም የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን ድብቅ የጥፋት አጀንዳ ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።
ቡድኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ፣ ወረራ፣ ግፍ፣ ሰቆቃና እየሆነ ያለውንእውነታ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴና ወዳጀ ሀገራት በግልጽ ማስረዳታቸው የታሰበው ሴራ ማክሸፍ ተችሏል፡፡
በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እውነታውን ተገንዝበው ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉ ሀገራትም ሊመሰገኑና በታሪክ ሊመዘገቡ እንደሚገባ የተናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ በሚችለው ልክ እውነታውን ለዓላም ማስረዳትና የሽብሩ ቡድኑን ተግባር ማክሸፍ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ሌላው የዩኒቨርሲቲው የሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልዩ ውዱ በበኩላቸው ፤ በእርዳታና በተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚዳፈሩና ፈር የለቀቁ አንዳንድ ሀገራት ድርጊታቸው ዓላማ ቢስ ነው ያሉት።
የአሸባሪውን የህወሓት ድብቅ አጀንዳ ለማስፈጸም አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ምክር ቤቱን ስብሰባ ቢጠሩም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅና ወዳጅ ሀገራት አልተሳካም ብለዋል፡፡
እንዲያውም ለሌላው የዓለም ህዝብ ቡድኑ የሚፈጽመውን ግፍና በደል በማስረዳት እውነታውን እንዲረዱ የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ለኢትዮጵያዊያን ድል መሆኑን ተናግረዋል።
አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት የጣልቃ ገብነት ሙከራው የውስጥ አንድነታችንን መላላትን አይተው እንደሆነ ጠቅሰው፤በዚህ ወቅት ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው አንድነታችን ጠብቀን ሉዓላዊነታችንና ነጻነታችንን ማስቀጠል ከሁላችንም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅነት መጠናከር እንዲሁም የህዳሴ ግድቡ መፋጠን የእግር እሳት ሆኖባቸው ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን ሙከራ በጋራ በመቋቋምና ወራሪውን ጠላት በመመከት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ጥቅም ማስጠበቅም ሀገራዊ ግዴታችን ነው።
''የዓለም ሀገራት አሸባሪው ቡድን ከትግራይ ክልል አልፎ በአማራና አፋር ክልሎች ንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን አስነዋሪ ተግባር አይተው እንዳላዩ ማለፋቸው ሳያንስ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር መሞከራቸው ተቀባይነት የሌለው ከንቱ ቅዤት ነው'' ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህር አቶ አደራጀው አለሜ ናቸው፡፡
ቡድኑ ጥርስ የነቀለበትን የተቀነባበረ ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው ድብቅ አጀንዳውን ለማስፈጸምና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚታትሩ ሀገራት ቢኖሩም በኢትዮጵያ ህዝብና ወዳጅ ሀገራት እየከሸፈ መሆኑን ተናግረዋል።
በፀጥታው ምክር ቤት የሰሞኑ ስብሰባ በኢትዮጵያ ላይ ተንኮል ለመሸረብ ቢሞከርም የሽብር ቡድን ጥፋት ከማጋለጥ ባለፈ ኢትዮጵያን ማንበርከክ እንደማይቻል በተግባር ያሳየ ነው።
አሁንም ሁሉም የኢትዮጵያ ምሁራን፤ ዲያስፖራውና ሌላውም ህዝብ እውነታው በማስረጃ ለዓለም በማሳየት ጣልቃ ገብነቱን መመከት ይኖርብናል ሲሉ አመልክተዋል።