የሐረርን ጥንታዊ ግንብ ጨምሮ በጎበኘኋቸው የተለያዩ ቅርሶች ተደንቄያለሁ -- ኬንያዊው አስጎብኚ - ኢዜአ አማርኛ
የሐረርን ጥንታዊ ግንብ ጨምሮ በጎበኘኋቸው የተለያዩ ቅርሶች ተደንቄያለሁ -- ኬንያዊው አስጎብኚ
ሐረር፣ ነሐሴ 25/ 2013 (ኢዜአ) የሐረርን ጥንታዊ ግንብ ጨምሮ የተለያዩ ቅርሶች ጎብኝቻለሁ ፤ በዚህም ተደንቄያለሁ ሲሉ ኬንያዊ የቱሪስት አስጎብኚ ተናገሩ።
ዳንኤል ካቶቦ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ ካሉ የኬንያ አስጎብኚ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃንን ከወከሉ አባላት መካከል አንዱ ናቸው።
የሐረር ሕዝብ ባህሉን ጠብቆ ከማቆየት እንዲሁም የሰላምና የመቻቻል እሴት ለሌሎች አካባቢዎችም መልካም ተሞክሮ ይሆናል ይላሉ።
ለኬንያውያን የኢትዮጵያን አስደናቂ ሥፍራዎችና እሴቶች እንደሚያስተዋውቁ ገልጸዋል።
ሌላዋ ኬንያዊት ፍሎረንስ ኪንግያንጉል "ኢትዮጵያ አስደናቂ ሀገር ነች፤ ሀገራችሁ በታሪክ የበለፀገችና በርካታ ሊታዩና ሊታወቁ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ይገኛሉ'' ብለዋል።
የሕዝቡ አቀባበልና መስተንግዶም አስደሳች እንደሆነ ገልጸው፣ በቀጣይም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለመምጣት እንደሚያስቡ ተናግረዋል።
ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቱሪዝም፣ የቢዝነስና ዲያስፖራ ጉዳዮች ሃላፊ አምባሳደር ዶክተር ደስታ ወልደዮሐንስ ፤ የሁለቱን ሀገራት ረጅም ዘመናት ያስቆጠረው ወዳጅነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በቱሪዝም ዘርፎች እየተጠናከረ መሄዱን ተናግረዋል።
በሀገራቱ እየተፈጠሩ ያሉትን ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም የላቀ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ ሀገሪቱ ያላትን መልካም ገፅታና የቱሪስት መስህቦችን በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቱሪዝም ኢትዮጵያ የቱሪዝም ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ወልደገብርኤል በርሄ ናቸው።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል በቱሪስት አመንጪ ሀገራት የሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶችን፣ መገናኛ ብዙሃንና ታዋቂ ግለሰቦችን በመጋበዝ መስህቦቹን ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ እንዲያስተዋውቁ ማድረግ ይገኝበታል ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለውን የቱሪስት ፍሰት እንደሚያሳድገው አቶ ወልደገብርኤል ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት አሰጎብኚ ድርጅቶች መካከል የገበያ ትስስርን በማጎልበት ወደ ምስራቅ አፍሪካ የሚመጡ ቱሪስቶች ሀገሮችን እንዲጎበኙ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
ቱሪዝም ኢትዮጵያ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማስተዋወቅን ዓላማው ያደረገ መርሃ ግብር እያካሄደ ነው።