ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የባህል ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው - የባህር ዳር በጎ ፈቃደኞች - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የባህል ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው - የባህር ዳር በጎ ፈቃደኞች
ባህር ዳር ነሀሴ 6/2010 ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በልማት ስራ ከመሳተፍ በተጨማሪ የባህል ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በባህር ዳር ከተማ የተሰማሩ የአገልግሎቱ ተሳታፊ ወጣቶች ተናገሩ። ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ 106 ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ትናንት ባህር ዳር ከተማ ገብተዋል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት ወጣቶች እንደገለጹት በሚቆዩባቸው 15 ቀናት ደም የመለገስ፣ ችግኝ የመትከል፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ የእንቦጭ አረምን በማስወገድና መስል በጎ አድራጎት ስራዎችን ያከናውናሉ፡፡ ከልማት ስራ በተጨማሪ የክልሉን የባህል እሴቶች በማወቅ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ ለሌሎች ለማሳወቅ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከትግራይ ክልል የመጣው ወጣት ማሃረ አሰፋ እንደገለጸው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በልማት ስራ ከመሳተፍ በተጨማሪ የአማራ ክልልን ህዝብ ባህልን፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ተፈጥሮአዊና ሰውሰራሽ መስህቦችን ለማወቅና ለማሳወቅ እድል ይፈጥራል፡፡ ''ከትናንት ጀምሮ የተደረገልን አቀባበል የአማራ ክልልን ህዝብ እንግዳ ተቀባይት ያስመሰከረ ነው'' ብሏል። ''የኢትዮጵያ ህዝቦች ተጠላልተው ሳይሆን ተነፋፍቀው እንደሚኖሩ የአማራ ከልል ህዝብ አቀባበል አስተምሮኛል'' ያለችው ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል የመጣችው ወጣት ስንቅነሽ ሲሳይ ናት። ከምታከናውነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ጎን ለጎን የአማራ ክልልን ባህል ለማወቅ እንደምትጥርና ያወቀችውን ለማሳወቅ አላማ ይዛ እንደመጣች ጠቁማለች። ''በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰውና ህዝቦችን ለመነጣጠል የሚደረገው የፖለቲካ ሴራ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደማይወክልና የኢትዮጵያ ህዝብ በፍቅር የተሳሰረ ለመሆኑ ከአማራ ክልል ህዝብ ተረድቻለሁ'' ብላለች። ወሰን ተሻጋሪ የበጎፈቃድ አገልግሎት የህዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር የሚያጠናክር በመሆኑ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባም ጠቁማለች፡፡ ለወጣቶቹ አቀባበል ያደረጉት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ እንደገለጹት የወጣቶች ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ማስቀጠያና “የመደመር” ጽንሰ ሃሳብ መገለጫ ነው። ወጣቶቹም የመጡበትን አላማ በአግባቡ በመረዳት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን ከማከናወን ጎን ለጎን ስለክልሉ በውጪ የሚወራውና መሬት ያለውን ነገር መረዳትና ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ''ወጣቱ ትውልድ ተጽኖ ፈጣሪና ተሰሚ እንደመሆኑ መጠን በህዝቦች መካከል ምንም አይነት መቃቃርና መጠላላት እንደሌለ ማስተማርና የተፈጠረው አገራዊ ለውጥ ፍሬ አፍርቶ ተጠቃሚ ለመሆን በርትቶ መስራት ይጠይቃል'' ብለዋል። ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ከሚያከናውኑት የልማት ስራ ጎን ለጎን ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች እንዲያውቁ የማስጎብኘት ስራ ይከናወናል ያሉት ደግሞ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ስቡዕ ገበያው ናቸው። ወጣቶቹ በትናንት ውሏቸው የባህርዳር አለም አቀፍ ስታዲየምን፣ የክልሉን ምክር ቤትና የአማራ ክልል ህዝቦች ሰማእታት ሀውልትን ጎብኝተዋል።