ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሓት ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ እየተመታ ነው

አዲስ አበባ ነሃሴ 25/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በከበባ እየተመታና እየተደመሰሰ መሆኑን የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

ኢትዮጵያን "ሲኦልም ቢሆን ገብቼ አፈርሳታለሁ" ብሎ የተነሳው አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ሰርጎ በመግባት ንፁሃንን በመግደልና ጉዳት በማድርስ ጥፋት ፈፅሟል።

አሸባሪው ሃይል በእብሪት በገባባቸው አካባቢዎች አሁን ላይ ከፍተኛ ምት እየደረሰበትና እየተደመሰሰ ይገኛል።

የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች እንዲሁም ማህበረሰቡ በሚያደርገው ትግል የአሸባሪው ሃይል አገር የማፍረስ ዓላማ ከሽፎ በየአካባቢው እየተመታ መሆኑን የመከላካያ ሰራዊት አመራሮች ገልጸዋል።

አሸባሪውን ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ሰራዊቱ በያለበት ሁሉ ኢትዮጵያን ለማዳን ግዳጁን በጀግንነትና በብቃት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የሃሰት መረጃዎችን በተላላኪዎቹ በኩል እያሰራጨ መሆኑን የሚነገሩት የጦር መሪዎቹ ህዝቡ የአሸባሪውን ቅጥፈት በመረዳቱ እየመከተውና ድል እያደረገው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአገር ህልውና ዘመቻው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በጀግንነት በየአውደ ግንባሩ አሸባሪው ሃይል በሞትና ሽሽት ላይ መሆኑን ጠቅሰው የመጠናቀቂያው ጊዜ እሩቅ አይሆንም ብለዋል።

አሸባሪ ቡድን በመደምሰስ ረገድ የታጠቀውም ያልታጠቀውም ህዝብ የሚያደርገው ድጋፍ እጅግ የሚያኮራና በግምባር ላለው ሰራዊት ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደሆነውም ተገልጿል።

ከሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ህዝቡ ግምባር ድረስ በመገኘት እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚደንቅ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም “በህዝባችን ብርቱ ድጋፍና ጠንካራ ደጀንነት አሸባሪውን ቡድን ወደ ሲኦል በማስገባት የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን አናደርጋለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም