ቀጥታ፡

አሸባሪውን የህወሃት ቡድን እና የእሱን ተላላኪ ኃይሎች በመደምሰስ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ይገባል

ነሀሴ 24/2013 (ኢዜአ) አሸባሪውን የህወሃት ቡድንና የእሱን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ የጥፋት ኃይሎችን በመደምሰስ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት አመራርና ሰራተኞች ገለጹ።

የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አመራርና ሰራተኞች በቢሺፍቱ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ- ግብር አካሄደዋል።

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉት የፓርቲው የፖለቲካና የርዕዮት-ዓለም ግንባታ ምክትል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ የአሸባሪው ህወሃት ቡድንና ድህነትን ድል በማድረግ ለመጪው ትውልድ የበለጸገች ሀገርን ማስረከብ ይገባል ብለዋል።

አሸባሪውን የህወሃት ቡድንና ፍላጎቱን ለማሳካት የሚሹ ኃይሎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ የኢትዮጵያን ሰላም ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

ዜጎች ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን በልማት ስራዎች ላይ መሳተፍ እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ልዩ ረዳት ሊያ ተከስተ በበኩላቸው በየደረጃው ያሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራርና ሰራተኞች የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን  ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠንካራ መሰረት መሆኑን በመገንዘብ በክረምቱ ወቅት በስፋት ሲተገበር መቆየቱንም አስታውሰዋል።

ከዚህ አኳያ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ችግኞችን እንዲተክልና እንዲንከባከብ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ነው የተናገሩት።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ የተሳተፉ የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች የሀገር ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚመጣን ኃይል በመመከት ለሀገር ብልጽግና መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች የወር ደመወዛቸውን ከመለገስ ጀምሮ ለመከላከያ ሠራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ሠራተኞች ከችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ በተጨማሪ በቢሾፍቱ ከተማ የጽዳት ዘመቻ አካሄደዋል።

በግብርና ሚኒስቴር፣ በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን፣ በተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን እና በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አስተባባሪነት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ አትሌቶች እና ታዋቂ ግለሰቦች በቢሺፍቱ ከተማ አረንጓዴ አሻራቸውን ማሳረፋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም