ቀጥታ፡

አባቶቻችን በነጻነት ያስረከቡንን ሀገር ህልውናዋን የመጠበቅ ግዴታ አለብን

ነሐሴ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) "አባቶቻችን በነጻነት ያስረከቡንን ሀገር ህልውናዋን የመጠበቅ ግዴታ አለብን" ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ፡፡

ሁሉም ዜጋ በጋራ በመተባበር በሀገር ህልውና ላይ ስጋት የደቀኑ አሸባሪዎችን መደምሰስ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።

ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ኢብራሂም ሲራጅ "አባቶቻችን መስዋዕትነት ከፍለው በነጻነት ያስረከቡንን ሀገር በአንድነትና በመተባበር ህልውናዋን መጠበቅ አለብን" ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል።

“የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝቦች በኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና አይደራደሩም” ያሉት አቶ ኢብራሂም፤ ህዝቡ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍ ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት ከመዝረፍ ጀምሮ በርካታ በደሎችን ሲፈጽም መቆየቱን አንስተዋል።

በህዝቦች ትግል በመጣው ለውጥ የክልሉ ህዝቦች በአገራቸው ጉዳይ በመሳተፍ የልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ መሃመድ አብዱራህማን በበኩላቸው በሀገር ክብርና ህልውና ላይ የሚመጣን ማንኛውም ኃይል ለመደምሰስ የሚደረግ ጥረትን እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡

"የሀገር ህልውናን ማስጠበቅ ካልተቻለ ሁሉም ነገር ዋጋ የለውም" ያሉት አቶ መሐመድ፤ አሸባሪው ህወሃትና ተላላኪዎቹ ሲቀርብላቸው የነበረውን የሰላም ጥሪ ሲገፉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የአገር ሽማግሌዎች በተደጋጋሚ ለሰላም የዘረጉትን እጅ በመግፋት ከኢትዮጵያውያን እሴት ያፈነገጠ ድርጊት መፈጸማቸውንም ተናግረዋል።

“በመሆኑም የሽብር ቡድኖቹ እያከናወኑ ያለውን ሀገር የማፍረስ ተግባር በጋራ ልንመክተው ይገባል” ብለዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊት የገንዘብ፣ የቁሳቁስ ድጋፍ ከማድርግ ባለፈ የክልሉ ወጣቶች የመከላከያ ሠራዊቱን እየተቀላቀሉ መሆኑንም የሀገር ሽማግሌዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም