በፀጥታው ምክር ቤት የሰሞኑ ስብሰባ የኢትዮጵያ እውነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በፀጥታው ምክር ቤት የሰሞኑ ስብሰባ የኢትዮጵያ እውነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል
ድሬዳዋ፣ ነሐሴ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ እውነት በዓለም አደባባይ ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገ ነው” ሲሉ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የህግ ምሁራን ተናገሩ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲፕሎማሲ ድል ለማግኘት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀጣይነት ያለው ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅበትም ተመላክቷል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ምሁርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ አሰፋ ካሳ፤ የምክር ቤቱ ስብሰባ ኢትዮጵያ የራሷን ጉዳይ በራሷ የመፍታት አቅምና ብቃት ያላት ሉአላዊነት ሀገር መሆኗን እንዳሳየ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላት እውነታ መጉላቱ የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በተደጋጋሚ ጊዜ ለውይይት ማቅረብ እንደሌለባት ያመላከተ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የአሸባሪውን ህወሓት ተፈጥሮና ሁለንተናዊ ባህሪ ለዓለም ህዝብና ለፀጥታው ምክር ቤት ተንትነው ማቅረባቸው ለእውነታው ደምቆ መታየት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
"በሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲ ሽፋን በአንዲት ሉአላዊት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ፍጹም የተሳሳተና የሽብርተኛው ህወሓት ደጋፊዎች የመጡበትን መንገድ ቆም ብለው እንዲገመገሙ ያደርጋል" ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አሰፋ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ሃብት ለምታ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ከፍታ ማረጋገጧ የማይቀር ነው።
"በሀገሪቱ ላይ የሚደረገውን የውስጥም ሆነ የውጭ ጫና እጅ ለእጅ በመያያዝ መሻገር የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል" ብለዋል፡፡
ሌላው በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ህግ ምሁር አለምሰገድ ደጀን ተመድ ለዓለም ሰላምና ፀጥታ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን እንደሚያይ ገልጸው፤ ነገር ግን የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ለማየት የሚያስችል የህግ መሰረት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
ስብሰባው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ታስቦ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጫናውን መነሻና መድረሻ በመገንዘብ አንዳንድ አገሮች በምክር ቤቱ መልካም ሃሳቦች በማንጸባረቃቸው የኢትዮጵያ እውነት ይበልጥ ጎልቶ እንዲታይ ማድረጉን ተናግረዋል።
ይህ እውነታ በቀጣይም ተቀባይነቱ እየጎለበተ እንዲመጣ ዲፕሎማሲያዊ ውይይትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
ለዚህ ደግሞ በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ ከተንቀሳቀሰ በዲፕሎማሲው የሚገኝን ድል እንደሚያፋጥነው ገልጸዋል።
በውጭና አገራት የሚገኙ ምሁራን፣ ዲፕሎማቶችና ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያን እውነት ዲጂታል ሚዲያን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ለማሳወቅ የጀመሩት ጥረት መጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል።