ጠላቶቻችንን አሳፍረን የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ታሪክ እንደግማለን- ወይዘሮ ሚስራ አብደላ - ኢዜአ አማርኛ
ጠላቶቻችንን አሳፍረን የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ታሪክ እንደግማለን- ወይዘሮ ሚስራ አብደላ
ሐረር ነሐሴ 24 / 2013 (ኢዜአ) ሀገር ለማፍረስ የተነሱ ጠላቶቻችንን አሳፍረን የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ታሪክ እንደግማለን ሲሉ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ አስታወቁ።
የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፋቸውን የገለጹበትንና አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ያወገዙበትን ህዝባዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
በሐረር ከተማ በተደረገው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የክልሉ የከተማና ገጠር ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተካፍለዋል፡፡
ሰልፈኞቹ የአሸባሪዎቹ ህውሃትና ሸኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው! ፤ አሸባሪ ሃይሎች ኢትዮጵያን እንዲያፈርሱ አንፈቅድም!፤ የጀግንነት ታሪክ እንጂ የባንዳነት ታሪክ የለንም! የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በማሰማት አሸባሪ ቡድኖቹን አውግዘዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በወቅቱ እንዳሉት የሽብር ቡድኖቹ ይዘው የተነሱት ሀገርን የመበታተን ዓላማ የራሳቸውን ፍላጎት እንጂ፤ የትኛውንም ብሔር አይወክልም።
"የክልሉ ነዋሪዎች ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በመሆን ሀገር ለማፍረስ የተነሱ ጠላቶቻችንን አሳፍረን የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ታሪክ እንደግማለን " ብለዋል ፡፡
በተለይም የትግራይ ሕዝብን ከአፍራሽ ሃይሉ በመነጠል ህወሃትን ከመሰረቱ ለመንቀል በሚደረገው ትግል ሚናችን እንወጣለን" ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ተናግረዋል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብዱጀባር መሐመድ በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሃትና ሸኔ የፈጠሩትን ጥምረት በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማቸውን እናመክነዋለን "ብለዋል፡፡