ሀገርን ለማዳንና ልማትን ለማስቀጠል ድጋፋችንን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
ሀገርን ለማዳንና ልማትን ለማስቀጠል ድጋፋችንን እንቀጥላለን
ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 24/2013 (ኢዜአ) ሀገርን ለማዳንና ልማትን ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን በመሆን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በድሬዳዋ የዑጋዝና አባገዳ ተወካዮች አስታወቁ።
ተወካዮቹ በድሬዳዋ በአራት የገጠር ክላስተሮች ያሉ 38 ቀበሌዎች ለመከላከያ ሠራዊት ያደረጉትን ድጋፍ ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት፣ ሀገርን ከተደቀነባት አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።
የኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ መሪ ዑጋዝ ተወካይ አቶ መሐመድ ሙሴ እንዳሉት፣ ሀገር በማፍረስ ተግባር የተሰማራውን የህወሓት ቡድን ለማስወገድ የኢሳ ማህበረሰብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በቀጣይም ያጠናክራል፡፡
የሶማሌ ህዝብ አንድ ጎሳ የሆነው የኢሳ ማህበረሰብ በጅቡቲ፣ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞንና በድሬዳዋ በዋናነት እንደሚኖር ጠቁመዋል።
ሀገርን ለማዳን የተጀመረው ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ ህዝቡን በማስተባበር የተጀመረው ድጋፍ እንደሚጠናከርም አቶ መሐመድ አረጋግጠዋል።
"ማህበረሰቡ የሀገራችን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ጅማሮ ለሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍም ይጠናከራል" ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር አባገዳ ተወካይ አቶ ሻሜ አብዱረህማን በበኩላቸው "ሀገር አፍራሹ የህወሓት ቡድን በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያደረሰው መከራና ግፍ፣ ግድያና ስደት ከሁሉም ህሊና የማይጠፋ ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው" ብለዋል።
ሸኔ ከዚህ ወንጀለኛና የሽብር ቡድን ጋር ህብረት ፈጥሮ የጀመሩት ሀገር የማፍረስ ተግባር በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድና አንድነት እንደሚመክንም ገልጸዋል፡፡
"ሀገርን ለማዳን የተጀመረው ዘመቻ እንዲሳካ በተለያየ መንገድ መደገፍ ብቻ አይደለም፤ እኔም ግንባር ለመዝመት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡
የጉርጉራ ማህበረሰብ ባህላዊ አባት ዑጋዝ ዚያድ ዳውድ በበኩላቸው፤ ማህበረሰቡን በማስተባበር ሀገርን ለማዳንና ልማትን ለማስቀጠል የሚያደርጉት ድጋፍና እገዛ እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል፡፡
"ሀገር የገጠማትን ወቅታዊ ችግር በድል ለመሻገር ከመቼውም ጊዜ በላይ ህብረትና አንድነትን ማፅናት ይገባል" ብለዋል።
የአሸባሪው ርዝራዦችና ተላላኪዎች ሠርገው ጥፋት እንዳያስከትሉ ሁሉም አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ዑጋዝ ዚያድ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡