ቀጥታ፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለባህል ማዕከል ግንባታ በአዲስ አበባ ቦታ ተረከበ

አዲስ አበባ ነሃሴ 24/2013 /ኢዜአ/ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለባህል ማዕከል ግንባታ በአዲስ አበባ ቦታ ተረከበ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሐሰን የማእከሉን የግንባታ ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተረክበዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በየጊዜው የገጠማትን ጠላት በህዝቦቿ አንድነት ድል በመምታት አንድነቷንና አኩሪ ታሪኳን ጠብቃ ኖራለች፡፡

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ወቅታዊ ፈተና በማለፍ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ትቀጥላች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በአሁኑ ትውልድም ተጠብቆ እንደሚዘልቅ ገልጸው አዲስ አበባም የሁላችን ባህላዊ እሴቶች የሚያንፀባርቁባት ከተማ እንድትሆን በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሐሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና በልጆቿ የጋራ ትግልና ፅናት ታልፈዋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ተደምስሰው ክብሯና ሉአላዊነቷ የተጠበቀች አገር ለትውልዱ እናስተላልፋለን ብለዋል።

በህዝቦች ትግል በመጣው ለውጥ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን አንስተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የክልሉ ህዝብ የባህል ማእከል እንዲገነባ ለሰጠው ቦታ አመስግነዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ኢትዮጵያ በርካታ አኩሪ ባህልና ታሪክ ያላት አገር በመሆኗ ይህንን ለማቆየትና ለትውልዱ ለማስተላለፍ የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦችን አቅፋ የያዘች ታላቅ አገር መሆኗን ጠቅሰው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የበርካታ የተፈጥሮዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች መገኛ በመሆኑ በአዲስ አበባ የባህል ማእከል እንዲኖረው መደረጉ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በመዲናዋ የሚገነባው የባህል ማዕከል የክልሉ ባህልና ታሪክ ይበልጥ እንዲታወቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።

የባህል ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ ሚኒስቴሩ ሙያዊ ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም