የሃገር መከላከያ ሰራዊት ሃገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ተልዕኮ ያፈራርሰዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሃገር መከላከያ ሰራዊት ሃገር ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን ተልዕኮ ያፈራርሰዋል
ደብረ ብርሃን ኢዜአ ነሀሴ 23/ 2013 ዓም የመከላከያ ሰራዊቱ ከአንድ ፖለቲካ ድርጅት ጠበቃነት ወጥቶ የኢትዮጵያ ህዝቦች ውክልና ያለው ሰራዊት በመገንባቱ ያጋጠመውን አደጋ በአጭር ጊዜ ይቀለብሰዋል ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አቶ ጌታቸው ሃይለማርያም ገለፁ።
''እኛ የሸዋ ወጣቶች ከሌሎች ወገኖቸ ጋር በመተባበር ከአባቶቻችን የተረከብነውን ታሪክና ማንነት በደምና አጥንታችን አስጠብቀን ለትውልድ እናስረክባለን'' በሚል መሪ ሃሳብ በደብረ ብርሃን ከተማ ውይይት ተካሄዷል።
ሚስትር ዴኤታው በውይይቱ እንዳሉት የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ በተባበረ ሃይል በመቀልበስ ለሀገራችን ብልጽግና መትጋት አለብን ብለዋል።
መከላከያ ሰራዊት ባለፉት 27 ዓመታት የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጠባቂ ሆኖ ተደራጅቶ በመቆየቱ በሃገር ላይ ሁለንተናዊ ጫና ሲፈጥር መቆየቱን ተናግረዋል።
አሁን ላይ መንግስት ችግሮችን በመለየት በወሰደው መልሶ ማደራጀት የኢትዮጵያ ህዝቦች ውክልና ያለው ሰራዊት መገንባት መቻሉን ገልፀዋል።
ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ እንዲደግም ሃገሩን ከውስጥና ከውጭ ወራሪ ሃይሎች ለመጠበቅ የግድ መደራጀት እንዳለበትም አመልክተዋል።
በዚህም ሙሉ ጤናማ የሆነ ወጣት በሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ በፌደራል ፖሊስና በአየር ሃይል በፈቃደኝነት በመቀላቀል ሃገሩን ማገልገልና እራሱንም ሆነ ቤተሰቡን ከአደጋ መጠበቅ እንዳለበት አብራርተዋል።
የህውሃት የሽብር ቡድን የደቀነውን የህልውና አደጋ በመመከትም የሃገሪቱን ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለማረጋገጥ ወጣቱ በሁሉም ዘርፍ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ በበኩላቸው በሽብር ቡድኑ የተጋረጠብንን ሀገር የማፍረስ አደጋ ለመቀልበስ የወጣቶች ሚና የላቀ ነው።
“ወጣቶች በማህበራዊ ሚድያ ከጠላት ወገን የሚደርሱ የውሸት ፕሮፖጋንዳዎችን በማጋለጥና አጀንዳውን ተገንዝቦ በመተንተን ህብረተሰቡን የማንቃት ስራ መስራት ይገባቸዋል” ብለዋል።
እንዲሁም ለሃገራቸው ህልውና ሲሉ የዘመቱ ወገኖችን ቤተሰቦች በኢኮኖሚ በመደገፍ ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የሸዋ የልማትና የሰላም ማህበር ሰብሳቢ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው በበኩላቸው የህውሃትና ሸኔ አሸባሪ ቡድኖች ህብረት ፈጥረው አገርን ለማፍረስ ከውጭ ሃይሎች ጋር እየሰሩ ነው”ብለዋል።
ቡድኖቹ በጋራ የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ዘረፋና አገር የማፍረስ ተልዕኳቸውን ለማክሸፍ ወጣቶች ተደራጅተው የህልውና ዘመቻው አካል መሆን እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
አሸባሪውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በመንግስት የቀረበውን የክተት ጥሪ መቀላቀሉን የገለፀው ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ደምስ ታከለ ነው።
በተጓዳኝ የክተት ጥሪውን ተቀብለው የዘመቱ ቤተሰቦችን በመከባከብና በመደገፍ ልማቱ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል እንደሚሰራም ተናግሯል።
በወቅታዊ የሰላምና ደህንነት ዙሪያ በተደረገው በውይይትም ከደብረ ብርሃን ከተማ የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።