በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ 50 በመቶ የጥምር እርሻ ፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብሩ 50 በመቶ የጥምር እርሻ ፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል
ነሃሴ 23/2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 50 በመቶ የጥምር እርሻ ፍራፍሬ ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር፣ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን፣ የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን፣ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የተገኙበት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ሳኒ ረዲ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ነው።
ለዚህም ተከታታይ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ጎን ለጎንም የአገሪቱን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከተተከሉ ችግኞች መካከል 50 በመቶው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የጥምር እርሻ ፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፍራፍሬ ችግኞችን የምግብ አቅርቦት ጥራት በማሻሻል የተመጣጠነ የምግብ ምርት እንዲገኝ እንደሚያስችሉና ጎን ለጎንም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትርና የአረንጓዴ አሻራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂኔር ስለሺ በቀለ፤ የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በጥሩ ሁኔታ እየተገባደደ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ አሻራው ተግባራዊ የተደረገው ኢትዮጵያዊያን የውስጥና የውጭ ጠላቶቻቸውን እየመከቱ መሆኑንም ገልጸዋል።
አትሌቶች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎችም በመርኃ ግብሩ ላይ መሳተፋቸውም ያለውን አገራዊ አንድነት ያሳያል ብለዋል።
የቢሺፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አለም ጸኃይ ሽፈራው፤ "የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የእናት ጡት ነካሽ የሆኑትን የወያኔና የሸኔ እየተዋጋን አሳክተነዋል" ብለዋል።
በመርኃ ግብሩ የተሳተፉ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና አትሌቶች በቀጣይ ተመሳሳይ መርኃ ግብር ላይ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በዘንድሮው "ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት" የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከ6 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው።