የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎችን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ማነፅ ይገባል-ሚኒስቴሩ

አዳማ ነሃሴ 23/2013 (ኢዜአ) የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥና የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎችን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ማነፅ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተደራጀን የሳይንስ፣ ሂሳብና ቴክኖሎጂ ትምህርት ማጠናከሪያ ማዕከልን ዛሬ ጎብኝተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በወቅቱ እንደገለፁት የትምህርት ጥራትን  በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ሂሳብ ላይ ተማሪዎቻችን ማነፅ ይገባል ።
በተለይ በአጠቃላይ ትምህርት ያሉ ተማሪዎች የሂሳብ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕውቀታቸው እንዲዳብር በሁሉም የሀገሪቷ ዩኒቨርስቲዎች ማዕከላትን ማደረጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"ማዕከላቱ ልዩ ተሰጦ ያላቸውን የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር ይኖርባቸዋል" ብለዋል ።
በዩኒቨርሲቲዎች የሚደራጁ የሳይንስ ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግና የሂሳብ ማዕከላት የሚመሩበት ማዕቀፍና የአሰራር መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግሯል ።
በአጠቃላይ ትምህርትም ሆነ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ማዕከላቱ የላቀ ሚና ያላቸው መሆኑን አመክተዋል ።
"በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂሪንግና በሂሳብ ማዕከል የተገኘውን ተሞክሮ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የጋራ በማድረግ በትምህርት ስርዓታችን ወጥነት ያለው ለውጥ ማምጣት አለብን " ብለዋል።
"የተማሪዎችን የሳይንስ ፍላጎት፣ ሚናና ልዩ ተሰጥፆ ለማዳበር ማዕከላቱ ቁልፍ ሚና አላቸው" ያሉት ደግሞ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ ናቸው ።
"የማስተማሪያ ስነ ዘዴ፣ የመምህራን የምዘና ብቃት፣ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት አጋዥነት አላቸው" ብለዋል ።
"ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማወቅ፣ ለሀገር ልማትና ዕድገት ለማዋል ዩኒርሲቲዎች በትብብር መስራት ይጠበቅብናል " ሲሉም አስገንዝበዋል ።
ማዕከሉ ከአዳማ ከተማና አካባቢዋ ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ልዩ ተሰጦ ያላቸውን 370 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዳማ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ አሸናፊ መንግስቱ በማዕከሉ ባገኘው ዕውቀት በፀሃይ ሃይል የሚሰራ የአነስተኛ የውሃ ፓንፕ መስራቱን ገልጿል።
የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ የሰብል ማጨጃ ማሽን በመስራት ለእይታ ያቀረበው ደግሞ በአዳማ የሃዋስ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12 ክፍል ተማሪ ሳሙኤል ታደሰ ነው።
በቀጣይ ማዕከላቱ በሁሉም የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በሚደራጁበት ሂደት ላይ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በትምህርታቸው የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች ዕውቅና ተሰጥቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም