ኢትዮጵያን ለማዳን እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ የሁሉም ርብርብ ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ለማዳን እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ የሁሉም ርብርብ ሊጠናከር ይገባል
ድሬዳዋ፣ ነሀሴ 23/2013 ( ኢዜአ) የአሸባሪውን ህውሓትና የውጭ ጠላቶች ተልዕኮ በማክሸፍ ሀገርን ለማዳን ሁሉም በአንድነት እያደረገ ያለውን ርብርብ ሊያጠናክር እንደሚገባ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የደቡብ ኪነ ጥበብ ቡድን በሁርሶ የኮንቲጀንት ማስልጠኛ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ምልምል የሰራዊት አባላት ታላቅ የማነቃቂያ ዝግጅት አካሂዷል፡፡
በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የሰላም ማስከበር የሎጀስቲክ ድጋፍ ሰጪ ስምሪት ኃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል ጠቅለው ክብረት በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳስታወቁት ሠራዊቱ መላውን ህዝብ ደጀን በማድረግ ሀገርን ለማሻገር እየተረባረበ ይገኛል፡፡
ሠራዊቱ ከልዩ ኃይሎችና ሚሊሻ ጋር በመሆን ሀገርን ለማፍረስ በተነሱ በህውሓትና በሸኔ ቡድኖች ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል ።
አሸባሪ ቡድኖቹን በመደምሰስ ሀገር ለማዳን የተጀመረው ዘመቻ በስኬት እንዲደመደም ሁሉም በአንድነት የጀመረውን ርብርብ ሊያጠናክር እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
አሸባሪው የህውሃት ቡድን በሠራዊቱ ላይ ያካሄደው የክህደት ወንጀል ሣያንሰው በማይካድራ፣ በአፋር ጋሊኮማና ሌሎች አካባቢዎች ያካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል በኢትዮጵያ ምድር ተደርጎ የማያውቅና መላውን ህዝብና ሠራዊት ቁጭት ውስጥ የከተተ መሆኑን አመልክተዋል።
"በህዝቡና በሰራዊቱ ዘንድ የተፈጠረው ቁጭት ዘመቻው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የሚያደርግ ይሆናል" ብለዋል፡፡
በተለይ ሀገር ለማዳን በየማሰልጠኛ ተቋሙ የሚገኙ የኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያት ትንታግ ወጣት ሰልጣኞች በቀሰሙት እውቀትና ጥበብ አሸባሪዎቹ ህውሃትና ሸኔ በፍጥነት እንዲደመሰሱ አቅም እንደሚሆኑ አመላክተዋል።
"ሰልጣኞች በጁንታ ሀይል ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የሀገራቸው አለኝታነታችሁን እንደሚያረጋግጡ አልጠራጠርም" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
በሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ የኮንቲጀንት ማስልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ በበኩላቸው" የውስጥና የውጭ ኃይሎች በመቀናጀት እየፈጸሙት ያለው ሀገር የማፍረስ ወንጀል በጀግኖች ልጆች ህብረትና አንድነት ይከሽፋል" ብለዋል፡፡
አሁን ላይ መላው ህዝብና ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነትና ኃይላቸውን አጠናክረው ሀገርን ለማዳን የጀመሩት ዘመቻ በስኬት እየተጓዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያ የገባችበትን ህግ የማስከበር እውነት እየተረዱት ይገኛሉ" ሲሉም ተናግረዋል ፡፡
ሀገርን ለማዳን የተጀመረው ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ በስንቅ፣ በገንዘብና ወጣቶችን ወደ ግንባር በመላክ የሚያደርገውን ድጋፍ ክልሉ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ በኪነ-ጥበብ ዝግጅቱ ላይ በእንግድነት የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የኪነ-ጥበባት፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ ናቸው፡፡
እሳቸው እንዳሉት የኢትዮጵያ ልጆች ከከፋፋይ ተግባራት በመራቅና አንድነትን በማጽናት የውስጥ ባንዳንና የውጭ ጠላትን ለማጥፋት መረባረብ አለብን፡፡
በስነ ስርአቱ ላይ የደቡብ የኪነ-ጥበብ ቡድን ለምልምል የሠራዊት ሰልጣኞች ላቀረበው ቀስቃሽ ዝግጅት ምስጋና ተችሮታል፡፡
ሰልጣኞኝ ምልምል የሰራዊት አባላትም ሀገራቸውን ከውጭም ሆነ ከውስጥ አሸባሪዎች ነጻ ለማውጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡