ሉዐላዊነትን በማስጠበቅ አኩሪ ገድል እየፈጸመ ላለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
ሉዐላዊነትን በማስጠበቅ አኩሪ ገድል እየፈጸመ ላለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል
ነሐሴ 23 ቀን 2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት በማስጠበቅ አኩሪ ገድል እየፈጸመ ለሚገኘው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከካቢኔ አባላት ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ጎበኝተዋል።ጉብኝቱ አየር ሀይላችን እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም እና ለውጥ ለማየት እና የከተማ አስተዳደር የሚችለውን ድጋፍ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኩራት የሆነውን የአየር ሀይላችን ከዚህ ቀደም ትኩረት ያልተሰጠው እና ከአቅሙ በታች ይሰራ የነበረ ተቋም መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ አሁን ላይ መሰረታዊ ሪፎርም ተደርጎለት በዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት በሚችል ደረጃ ላይ መሆኑን መመልከት ችለናል ብለዋል።
የአየር ሀይሉ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት በማስጠበቅ አኩሪ ገድል እየፈጸመ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።የከተማ አስተዳደሩም ለአየር ሀይል አባላት ደጀንነቱን ለመግለጽ የሰንጋ በሬዎችን ድጋፍ አድርጓል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል በተካሄደው የጉብኝት መርሐግብር የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና የካቢኔ አባላት መሳተፋቸውን የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢሮ አስታውቋል።