የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ የድርሻውን ይወጣል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23/2013 (ኢዜአ) የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ ከመንግስት ጋር በመቆም የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ገለጸ።

የፓርቲው አመራሮች ከአባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ከራያ አካባቢ ተወላጆች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም አሸባሪው ህወሓት ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በራያ ህዝብ ላይ በተለየ መልኩ ከፍተኛ በደል አድርሷል፣ ገድሏ፣ አፈናቅሏልም ብለዋል።

በመሆኑም የህወሓት የሽብር ቡድን ለራያም ይሁን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የማይበጅና አገር አፍራሽ ሃይል በመሆኑ ተደምስሶ እስከ ወዲያኛው ሊጠፋ ይገባል ነው ያሉት።

በዚህ ሂደት ራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አሸባሪውን ለመደምሰስ ከመንግስት ጋር በመቆም የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

መንግስት የተናጠል ትኩስ አቁም ባደረገበት ወቅት አሸባሪው ህወሃት ቀድሞ ጥቃት ካደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል የራ ህዝብ መሆኑን ጠቁመው ህዝቡም በሚችለው መልኩ ሊከላከል ሞክሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎችን በመግደልና በማፈናቀል ከፍተኛ በደል መፈፀሙን አንስተዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ካሳው ቢሻውና አቶ ተስፋዬ አራጌ፤ ይህ አሸባሪ ቡድን ካልጠፋ ከኢትዮጵያም አልፎ ለአካባቢው አገራት የሰላም ጸር መሆኑ አይቀሬ ነው።

በመሆኑም የሽብር ቡድኑን ለማስወገድ ማንኛውንም መስዋእትነት በመክፈል የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እናረጋግጠለን ብለዋል።

የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሴቶች አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ ሸዋዬ በሪሁን፤ አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ ግለሰብ ከመንግስት ጎን ቆመናል ብለዋል።

ቡድኑን ለማጥፋት እስከ ጦር ግንባር በመዝመት ለመፋለም ተዘጋጅተናል ሲሉም አረጋግጠዋል።

"የፓርቲያችን ስራ አስፈጻሚ አባላት በግንባር የበኩላቸውን እየደረጉ ነው" ሲሉም ሃላፊዋ ገልጸዋል።

የፓርቲው የድርጅት ኃላፊ ዶክተር ጌታቸው መኮንን በበኩላቸው የህወሓት የሽብር ቡድን መዋቅራዊ  በደል በራያ ህዝብ ላይ መድረሱን ጠቁመው አሁን የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ የበኩላችን እንወጣለን ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ሰርጎ በመግባት ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ባደረሰው ውድመት ጉዳት የገጠማቸውን ዜጎች በመደገፍ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም