የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ለሠራዊቱ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ለሠራዊቱ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለገሱ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የአገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ለሚዋደቀው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ለገሱ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተያዘው ዓመት መጨረሻ አጠቃላይ ኃብቱ 1 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር መድረሱም ተገልጿል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ባንኩ ከዚህ ቀደም 300 ሚሊዮን ብር ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
በዛሬውም ዕለት ደግሞ የባንኩ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት የአንድ ወር ደሞዛቸውን በድምሩ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ መለገሳቸውን ገልጸዋል።
ድጋፉም ለመከላከያ ሠራዊትና ለክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁ የማኅበረሰበ ክፍሎች የሚውል ነው ብለዋል።
ግንባር ለመሄድ ለወሰኑ የባንኩ ሠራተኞችም ባንኩ ደሞዛቸውንና ጥቅማጥቅማቸው እንዲከበርና ለቤተሰቦቻቸው አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።
እስካሁንም አራት የባንኩ ሠራተኞቹ ወደ ግንባር መሄዳቸውን በመጠቆም።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ኃብት 1 ነጥን 1 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ገልጸው በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ካሉ ባንኮች መካከል ትሪሊየን ኃብት በመፍጠር ሁለተኛው ባንክ መሆኑን ገልጸዋል።
የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ ከ140 ቢሊየን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለበት ዓመት እንደነበርም ጠቁመዋል።
ባንኩ ከ20 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ዓመታዊ ትርፍ ማስመዝገብ እንደቻለም ተናግረዋል።
በቀጣይም ባንኩ የሚጠበቅበትን ማኅበራዊ ኃላፊነት በመወጣት የአገሪቱን ልማት ለማስቀጠል እንደሚተጋ ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።