ከ37 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ከ37 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል
አርባ ምንጭ፣ ነሐሴ 23/2013 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ37 ሺህ በላይ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአርባ ምንጭ ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የ2013 ዕቅድ አፈጻጸምና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ ተጠናቋል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሊቶ እንዳስታወቁት ሚኒስቴሩ በ2013 በጀት ዓመት በዋናነት በአሠሪና ሠራተኛ እንዲሁም በማህበራዊ ደህንነት ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ተንቀሳቅሷል።
በተለይ በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት 37 ሺህ 932 ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን ጠቅሰዋል
በዘርፉ ከተሰጠው አገልገሎትም 19 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።
የስራ ስምሪቱ የተደረገው በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፣ ኳታር፣ ጆርዳንና ሳዉዲ አረቢያ መሆኑን ጠቁመው በሀገራቱ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ጋር በተደረገ መናበብ ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው በ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ
ለ2 ሚሊዮን ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እቅዱን ለማሳካት በተለይ የህዝብና የሀገር ሃላፊነት ተሰምቷቸው የሚሠሩ ኤጀንሲዎች እንዳሉ ሁሉ ለህግ ተገዠ ያልሆኑ በርካታ ኤጀንሲዎች በመኖራቸው ችግሩን ለመፍታት እየሰራን መሆናቸውን ተናግረዋል።
በህጋዊ መንገድ ወደ ዉጭ ሀገር የሚደረጉ የሥራ ሥምሪቶች ዜጎች የባህር ዓሣ ሲሳይ ከመሆንና ከሚደርስባቸው የተለያዩ አደጋዎች የሚታደግ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
"ምንም እንኳን በውስጥም ሆነ በውጭ እየገጠመን ያለው ሳንካ ቢያደናቅፈንም ኢንዱስትሪው እየተስፋፋ በመሆኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አሠሪዎችና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሠራተኞች የሥራውን ዓለም የሚቀላቀሉበት ወርቃማ ጊዜ ላይ ናቸው" ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ጨምሮ የአስፈጻሚ አካላትን ተግባር በመከታተልና በመቆጣጠር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በምክር ቤቱ የሴቶች፣ የወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ ናቸዉ።
ከውጭ ሀገር ስምሪት ጋር በተያያዘ በአዋጅ ቁጥር 923/2011 ማዕቀፍ ውስጥ ለውጡን አዝጋሚ የሚያደርጉ አንቀጾች ተለቅመው ማሻሻያ መደረጉን አመልክተዋል።
አዋጁን ተፈጻሚ ማድረግ የዜጎችንን ደህንነት ከማስጠበቅ በላይ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አጽንኦት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
የደቡብ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀልጌዮ ጁሎ በበኩላቸው የአሠሪም ሆነ የሠራተኛው መብቶች በአግባቡ እየተጠበቁ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ምቹ ሀገራዊ የስራ ሁኔታ በመፍጠር ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመዋል።
በተለይ በተሻሻለው የሀገር ውስጥ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ መመሪያ መሠረት ፍቃድ የወሰዱ ኤጀንሲዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡና በሂደቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ ከሁሉም ክልሎች የዘርፉ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በአርባ ምንጭ ማረሚያ ቤት ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን የተሃድሶ ማዕከልንም ጎብኝተዋል።