የምግብ ዘይት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዘይት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው
ባህር ዳር፣ ነሐሴ 23/2013 (ኢዜአ) በገበያ ላይ የተከሰተውን የምግብ ዘይት የዋጋ ንረት ለማረጋጋት 24 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዥ መፈፀሙን የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የኑሮ ውድነትን መከላከል በሚያስችሉ አሰራሮች ዙሪያ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ በውይይት መድረኩ ላይ እንዳሉት ድርጅቱ በሀገር ደረጃ የተመረጡ ምርቶችን በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት እየሰራ ይገኛል።
ድርጅቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በ34 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ ገበያ የተገዛ የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ላይ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
ከውጭ ወደ ገሀር ውስጥ እየገባ ያለው 24 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በሁሉም ክልሎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ እንደሚዳረስ አስታውቀዋል።
"መንግሥት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያቀርባቸውን የምግብ ዘይትና ሌሎች ምርቶች በትክክል ለተጠቃሚው ማህበረሰብ እንዲደርስ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን እንቅስቃሴ በጋራ መከላከል ይገባል" ብለዋል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ውቤ በበኩላቸው ህብረተሰቡ
ምርት በመጋዘን በመደበቅ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ ስግብግብ ነጋዴዎችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት እንዲተባበር ጠይቀዋል።
አሸባሪውን ህወሓት እየታገልን ባለንበት በዚህ ውስብስብና አስቸጋሪ ወቅት መደጋገፍ ሲገባን ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህብረተሰቡን ማማረር ወንጀል መሆኑን አስገንዝበዋል።
"የግብይት ስርዓቱ እንዲናጋ እያደረጉ የሚገኙ ነጋዴዎችን በመለየት ለህግ እንዲቀርቡ ይደረጋል" ብለዋል።
ምርትን በመደበቅና እጥረት በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ አቶ ንብረት ባንቲገኝ ናቸው።
ምክር ቤቱ በአቋራጭ ለመክበር ዋጋ የሚያንሩ ነጋዴዎችን ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብና ለማስተካከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ የባህር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አቢይ መለሰ ኮርፖሬሽኑ ከ30 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ሥራ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።