የአረንጓዴ አሻራ ትግበራው የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችም ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ትግበራው የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችም ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ ትግበራው የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችም ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ የሚያደርግ መሆኑን የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
''ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት'' የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ አትሌቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በቢሾፍቱ ከተማ ችግኞችን ተክለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ እያሳረፍነው ያለው የአረንጓዴ አሻራ ለህዳሴ ግድባችን ዘለቄታዊ ጥቅም ትልቅ አበረክቶ አለው ብለዋል።
ችግኞች እየተተከሉ ኢትዮጵያ አረንጓደ ስትሆን ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችም ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ያደርጋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማስጠበቅ የአካባቢ መራቆትን በመታደግና ምቹ አካባቢ በመፍጠር እንዲሁም የብርቅየ አራዊቶችን መሰደድ ለማስቆም እየሰሩ እያደረጉት ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት አገር በቀልና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች በብዛት እየተተከሉ መሆኑም ተጨማሪ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
የሚተከሉ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከመስጠታቸው ባሻገር ኢትዮጵያ የተሻለ አየር፣ በቂ የገጸ-ምድር፣ የምንጭና የከርሰ ምድር ውሃ እንድታገኝ ያስችላል ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ኢትዮጵያን ዓለም አቀፉን አየር ንብረት ለውጥ በመቀልበስ ተምሳሌት አድርጓታል ነው ያሉት።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በኢትዮጵያ 6 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ተይዟል።
በጎረቤት አገራት ደግሞ 1 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡