ሁሉንም የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ሀገርን መታደግ ይኖርብናል - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉንም የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ሀገርን መታደግ ይኖርብናል
መቱ፣ ነሐሴ 23/2013 (ኢዜአ) ሁሉንም የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለሕዝቡ በማድረስ ሀገርን መታደግ ይኖርብናል ሲሉ የኢሉባቦር ዞን የመንግስት የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ገለፁ።
ባለሙያዎቹ የ2013 ዓ.ም የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት መድረክ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል።
ባለሙያዎቹ "ሳይኖሩ አለን፣ እየሞቱም እናሸንፋለን" በማለት የሐሰት ፕሮፓጋንዳቸውን በሚነዙት ባንዳዎች ወሬ ሕብረተሰቡ እንዳይደናገር ትክክለኛ መረጃን ከትክክለኛው ምንጭ በጊዜው ለማድረስ በዞኑ ከሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኖኖ ወረዳ ሪፖርተር ተስፉ ደባስ "ኅብረተሰቡን በሐሰት መረጃ ከመደናገር ለመጠበቅ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለሕዝቡ ማድረስ ይገባናል" ብሏል።
ሕብረተሰቡ በየደረጃው ሰላምን በማስጠበቅ ላይ መሥራት እንዳለበት ተናግሯል።
"የእርስ በርስ ጠላቶች እንደነበሩ ሲያስመስሉ የነበሩት አሸባሪዎቹ ሸኔና ሕወሓት ሀገርን ለማፍረስ የመሰረቱት ስምምነት የመጨረሻ ዝቅጠታቸውን ያሳየ ነው" ያለው ደግሞ የሀሉ ወረዳው ሪፖተር ምትኩ ታከለ ነው።
"ቡድኖቹ የፈጸሙት ስምምነት በታሪክ መቼም የማይረሳ በሀገር ላይ የተፈፀመ ክህደት ነው" ያለው ባለሙያው "ሀገርን የማፍረስና የብሔር ብሔረሰቦችን የዕድገት ተስፋ ለማጨናገፍ የተነሱትን አሸባሪ ኃይሎች ሴራ አስከ መጨረሻው ለማክሸፍ በሁሉም መንገድ እንታገላለን" ብሏል።
የአሌ ወረዳ ሪፖርተር ወገኔ ታምራት በበኩሏ "ሕወሓትና ሸኔ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ የአንድ ወይም የተወሰኑ ብሔሮች ብቻ ጠላት አይደሉም" ትላለች።
"ሀገር የሁሉም ስለሆነች ሁሉም ዜጋ የሀገርን ጠላት ለመመከትና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በጋራ ሊቆም ይገባል" ብላለች።
"ሳይኖሩ አለን፣ እየሞቱም እናሸንፋለን" በማለት የሐሰት ፕሮፓጋንዳቸውን በሚነዙት ባንዳዎች ወሬ ሕብረተሰቡ እንዳይደናገር ትክክለኛ መረጃን ከትክክለኛው ምንጭ በጊዜው በማድረስ ላይ በቅንጅት ለመስራት ባለሙያዎቹ ዳግም ቃል ገብተዋል ።
የኢሉባቦር ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እሸቱ አረጋ በበኩላቸው "ሀገርን ከጠላት ለመታደግና የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በተለይም የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ለማስቀጠል የትክክለኛ መረጃ ጉዳይ ወሳኝ ነው" ብለዋል።
ሕብረተሰቡን በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ከመደናገር ለመጠበቅ ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ማድረስ እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊው በዞኑ ያሉትን መገናኛ ብዙኃን በማቀናጀት በጉዳዩ ላይ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።