የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር 'የኢትዮጵያ አንድነት ዋንጫ' በሚል ውድድር ሊያካሂድ ነው

114

ነሀሴ 22 ቀን 2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር 'የኢትዮጵያ አንድነት ዋንጫ' በሚል ውድድር እንደሚያካሂድ አስታወቀ።

አክሲዮን ማኅበሩ ከ23 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ለማካሄድ መዘጋጀቱንም ዛሬ ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ገልጿል።

የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ  'የኢትዮጵያ አንድነት ዋንጫ' በጥር 2014 ዓ.ም ሐዋሳ ላይ እንደሚካሄድ ለኢዜአ ገልፀዋል።

በውድድሩ ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከሰሜን፣ ከደቡብ የአገሪቷ አካባቢዎችና ከአዲስ አበባ የሚውጣጡ ቡድኖች ይሳተፋሉ።

ለውድድሩ የተመረጠው ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የሚሳተፍበት ወቅት እንደሆነም ጠቁመዋል።

የቡድኖች፣ የአሰልጣኞችና የተጫዋቾች ዝርዝር መረጃ የውድድሩ ጊዜ ሲቃረብ እንደሚታወቅና ውድድሩ እንዲካሄድ ውሳኔ የተላለፈው በጠቅላላ ጉባኤው አባላት ይሁንታ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ ዜና አክሲዮን ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤው በወሰነው መሰረት ከ23 ዓመት በታች የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ሊያካሂድ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ አስታውቀዋል።

በውድድሩ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በላይ እና ከ23 ዓመት በታች የሆኑ ተጫዋቾች እንደሚካተቱ ነው የገለፁት።

ከ17 ዓመት በታች ለማድረግ የታሰበው የታዳጊዎች ውድድር ግን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመወያየት እንደሚወሰን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማኅበር በዛሬው 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው በ2014 ዓ.ም ከተመልካች የሚገኘውን ገንዘብ ክፍፍል ሁኔታ አሳውቋል።

በዚሁ መሰረት ከተመልካች ከሚገኘው ገቢ ለሜዳ ድጋፍ 10 በመቶ፣ ለባለ ሜዳው ክለብ 80 በመቶ፣ ለአክሲዮን ማኅበሩ 10 በመቶ  እንደሚከፋፈል ይፋ አድርጓል።

የስታዲየም መግቢያ ትኬት ዋጋ ክፍያም 1ኛ ደረጃ 300 ብር፣ 2ኛ ደረጃ 200 ብር፣ 3ኛ ደረጃ 100 ብር፣ 4ኛ ደረጃ 50 ብር መሆኑን አስታውቋል።

ወደ ስታዲየም የሚገባው ተመልካች ውድድሩ የሚከናወንባቸው ስታዲየሞች ከሚይዙት የሰው ቁጥር አንድ አራተኛው ብቻ እንደሚሆንም ተወስኗል።

ለባለሜዳው ክለብ 70 በመቶ ለእንግዳ ክለብ 30 በመቶ ደጋፊዎች እንደሚገቡም ተገልጿል።

ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይን በተመለከተም 16ቱ ክለቦች እያንዳንዳቸው 500 ሺህ ብር በድምሩ 8 ሚሊዮን ብር ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል።

ክለቦቹ ገንዘቡን የሚሰጡት ከሚያገኙት የብሮድካስቲንግ እና የስፖንሰር ገቢ በመቀነስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም