በጋምቤላ 171 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ይካሔዳል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ 171 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ይካሔዳል

ጋምቤላ፤ ነሀሴ 22/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ በፌዴራል መንግስት ድጋፍ ከ170 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር በሚበልጥ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ሊካሄድ ነው።
የንጹህ መጠጥ ውሃ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ግንባታ በፌዴራል የውሃ ልማት ኮሚሽንና በክልሉ ውሃና መስኖ ልማት ቢሮ ትብብር እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በፌዴራል ውሃ ልማት ኮሚሽን የኮንትራት ማኔጅመንት ስፔሻሊስት አቶ ብሩክ ኃይለየሱስ ዛሬ የሳይት ርክክቡ ሲካሄድ እንዳሉት የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚካሄደው በከተማው በዝቅተኛ ደረጃ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ ነው።
በፕሮጀክቱ ከሚናወኑት ሥራዎች መካከል የሁለት ታንከር ግንባታ፣ የ13 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ማሻሻልና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹ ቀደም ሲል በከተማው በቀን 6 ሺህ ሜትር ኪዩብ የነበረውን የውሃ የማምረት አቅም ወደ 7 ሺህ ሜትር ኪዩብ ከፍ እንደሚያደረገው ገልጸዋል።

አዲስ የሚገነቡት ታንከሮች ቀደም ሲል የታንከሮች የመያዝ አቅም 1 ሚሊዮን 500 ሺህ ሊትር የነበረውን ወደ 2 ሚሊዮን ሊትር እንደሚያሳድገውም አስገንዝበዋል።
በከተማው በ170 ሚሊዮን 705 ሺህ ብር ወጪ የሚካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ከነሐሴ 22 ቀን 2013 ጀምሮ በአስር ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃም ጊዜ መቀመጡን አቶ ብሩክ ተናግረዋል።
የክልሉ ውሃና መስኖ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊዌ የፌዴራል ውሃ ልማት ኮሚሽን በከተማው የሚያታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ላደረገው ድጋፍና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፕሮጀክቱ በተለይም በከተማው ቀበሌ 01 እና 05 የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታ ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ አስፋላጊው ድጋፍና ትብብር ይደረጋል ብለዋል።
የሥራ ተቋረጩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ታገሰ በበኩላቸው የከተማው ማህበረሰብ መልካም ትብብርና ደጋፍ ካለ ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ሰርተው እንደሚያስረከቡ አረጋግጠዋል ።