ቀጥታ፡

ለሀገር አንድነት ዘብ በመቆም የአባቶቻችንን አደራ እንወጣለን

ሚዛን ፤ ነሀሴ 22/2013 (ኢዜአ) ለሀገር አንድነትና ለህዝብ ሰላም ዘብ በመቆም የአባቶቻችንን አደራ እንወጣለን ሲሉ የሚዛን አማን ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

በወጣቶቹ አስተባባሪነት ዛሬ በከተማዋ አሸባሪ ቡድኖችን የሚቃወም ፣ መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላትን የመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ሚዛን አማን በተካሄደበት ወቅት ወጣቶች ባላቸው አቅም ሁሉ የጥፋት ሀይሎችን በመታገል የሀገርና የህዝብ ክብርን የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል  ወጣት አሰገደች ወልዴ አንዷ ስትሆን፤  በሀገርና በህዝብ ህልውና ላይ የመጣን ኃይል መታገስ በታሪክ ያስወቅሳል ስትል  ለኢዜአ ተናግራለች።

እንደ ወጣት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም በቻለችው አቅም ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷን ነው የገለጸችው።

"ወንድሜ በመዝመቱ ደስተኛ ነኝ፤ ቢሞት እንኳ አልቆጭም፤ ምክንያቱም ስለ ሀገር ታግሎ መሞት ክብር ነውና" ያለችው ወጣቷ፣ ለሀገሯ ዘብ በመቆምና ጠንክራ በመታገል የአባቶቿን አደራ  እንደምትወጣ አስታውቃለች።

"እኛ እዚህ የቀረን በግንባር መዋጋት ባንችል እንኳ ከሠራዊቱ ጎን ሆነን ስንቅ ብናቃብልና ደም ብንለግስ ትልቅ ድል ይገኛል" ብላለች።

ሌላው ወጣት ዘሪሁን ዘውዴ "ለእናትና ለሀገር የማይኮን ነገር የለምና ስለ እናት ሀገር ኢትዮጵያ ሁሉንም እሆናለሁ" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ መዝመት እንጂ መደራደር አናውቅም ያለው ወጣቱ "ግንባር ላይ እየተፋለሙ ያሉትን በገንዘብና ደም በመለገስ እየደገፈ መሆኑን ተናግሯል።

"አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለመዝመት ቁርጠኛ ነኝ" ሲልም ነው አጋርነቱን ያረጋገጠው።

ሁሉም ሀገራዊ አደራ እንዳለበት የገለጸችው ወጣት ህይወት መለሰ "በአባቶቻችን ደምና አጥንት ሀገር ሳትደፈር ቆይታለች፤  እኛም የተሰጠንን ሀገር ለትውልድ የማስተላለፍ አደራ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብላለች።

አሸባሪዎች ተደምስሰው በኢትዮጵያ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ እንደ ወጣት ባላት አቅም ሁሉ ሀገሯን ለማገልገል መዘጋጀቷንም ተናግራለች።

"በህወሓት ፕሮፓጋንዳ ተስፋ ቆርጠንና እጅ እግር አጣጥፈን የምንቀመጥ አይደለንም" ያለው ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ፈለቀ ኩይክ ነው።

"ግንባር የሄዱ ወንድሞቻችንን እያሰብን በገንዘብ፣ ደም በመለገስና በሞራል ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ብሏል።

ወጣቱ እንዳለው፤ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በአካባቢው ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱትን ተከታትሎ በመያዝ ለህግ የማቅረብ የበኩሉን እየተወጣ ነው።

የቤንች ሸኮ ዞን ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እምቢያለው ኃይለኢየሱስ፤ ወጣቶች የአሸባሪዎችን ዕድሜ ለማሳጠር ከጫፍ እስከ ጫፍ መነሳታቸውን አስታውቋል።

ከድጋፍ ሰልፉ በኋላ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አባላት ደም መለገሳቸውን ነው የገለጸው።

"እኛ በህይወት ቁመን ኢትዮጵያ በሽብርተኞች አትፈርስም" ያሉት ደግሞ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሠ ካተመራሻ ናቸው።

በቅርቡ በተጀመረው ሁለተኛ ዙር የወጣቶች ምልመላ 180 ወጣቶች በፍላጎት ለመዝመት መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም